ጥንታዊ ጽሑፎችን ለመጠበቅ በቅንጅት መሥራት እንደሚገባ ተገለጸ
- Details
- Created on Thursday, 11 December 2014 12:04
- Written by ቀዳሚ ገጽ
ታኅሣሥ 2 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
ጥንታዊ ጽሑፎችን ለመጠበቅና ለተከታዩ ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል ባለ ድርሻ አካላት በቅንጅት መሥራት እንደሚገባቸው ኅዳር 29 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ በቀረቡ ጥናቶች ተገለጸ፡፡
በእለቱ ሦስት ጥናታዊ ጽሑፎች የቀረቡ ሲሆን፤ “በጥንታዊ ጽሑፍ ሃብቶች አጠባበቅና አያያዝ ላይ የሚታዩ ችግሮችና ተግዳሮቶች” በሚል በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር በአቶ አብርሃም ጮሻ፤ “የጥንታዊ ጽሑፎችን በመጠበቅ ለአገልግሎት ማዋል” በአቶ ተስፋዬ ካሱ፤ “የጽሑፍ ቅርሶችን መለየትና መመዝገብ” በአቶ ዮሴፍ ደምሴ የቀረቡ ጥናቶች ናቸው፡፡
የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ አብርሐም ጮሻ ባቀረቡት ጥናት በሥነ ጽሑፍ ሃብቶች አጠባበቅና አያያዝ ላይ የሚታዩ ችግሮችና ተግዳሮቶችን በማስመልከት ኤጀንሲው ከተመሠረተ 71 ዓመታትን ቢያስቆጥረም ከተሰጠው ተልእኮ አንጻር ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ቅንጅት መፍጠር ያለመቻሉ በዋነኛነት እንደ ችግር ጎልቶ የሚታይ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ኤጀንሲው በሥነ ጽሑፍ ሃብቶች አጠባበቅ ረገድ አገራዊ ይዘትና ቅርጽ ለመፍጠር መዘግየቱን፤ በዘመናዊ መልኩ የተደራጀ አለመሆኑ፤ ጥሩ የጥበቃ ሥርዓት አለመኖሩ፤ አገራዊ አቅጣጫ ማስቀመጥ አለመቻሉ፤ ወቅቱ ለሚጠይቀው ደረጃ ራሱን ያላበቃ መሆኑ፤ የአገልግሎቱ ተደራሽነት በማስፋፋት ረገድ ውሱንነቶች መስተዋላቸው እንደ ችግር ካነሷቸው ነጥቦች ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡
አቶ አብርሃም በጥናታቸው የመፍትሔ አቅጣጫዎችንም ዳስሰዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አገራዊ የተደራጀ መዋቅራዊ የሕግ ሥርዓት መዘርጋት፤ አገራዊ የሆነ የሁሉም ባለ ድርሻ አካላት ቅንጅታዊ መማክርት መመሥረት፤ የግንዛቤ ማሳደጊያ ሥራዎችን ትኩረት ሰጥቶ መሥራት፤ ሃብቶቹን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ለባለ ድርሻ አካላት ወጥነት ያለው ስልት መቅረጽና መዘርጋት፤ በሁሉም ደረጃ ዘመናዊ የጥበቃ ሥርዓት መዘርጋት፤ ተጠባባቂ ክምችቶችን ማዘጋጀትና ማደራጀት እንደ መፍትሔ አቅርበዋል፡፡
“ጥንታዊ ጽሑፎችን በመጠበቅ ለአገልግሎት ማዋል” በሚል ርዕስ በአቶ ተስፋዬ ካሱ የቀረበው ጥናታዊ ጽሑፍ ጥንታዊ ጽሑፎችና መረጃዎችን ለትውልድ በማስተላለፍ ረግድ ያለውን ጠቀሜታ ሲገልጹ፡- የታሪክና የባሕል ሽግግር ለማድረግ፤ ሥነ ሃይማኖታዊ ትምህርት ለመስጠት፤ ለመድኃኒትነት የተጻፉትን ጥናትና ምርምር ለማድረግ፤ ሥነ ፍጥረት ላይ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ እገዛ ለማድረግ እንደሚረዱ ጠቁመዋል፡፡
የአገራችን የጥንታዊ ጽሑፎች አጠባበቅ ምን እንደሚመስል ሲዳስሱም አባቶቻችን እስከ ዛሬ ድረስ አቅማቸውን የፈቀደውን ሁሉ አድርገው ለዛሬው ትውልድ እንዲደርሱ ማድረጋቸው እውቅና ሊሰጠው የሚገባው ታላቅ ሥራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፤ ሆኖም በተለያዩ ቦታዎች ጥንታዊ ጽሑፎች ተበታትነው መቀመጣቸው፤ በግለሰቦች ቤት ውስጥ አመቺ ባልሆነ ስፍራ ላይ መከማቸታቸው፤ በጦርነትና በስርቆት ከአገር በሕገ ወጥ መንገድ መውጣታቸው፤ ያሉትም በዋሻዎች ውስጥ ምቹ ባልሆነ ቦታ በመቀመጣቸው ለአቧራ፤ ለተለያዩ ተባዮችና ለእርጥበት የተጋለጡ በመሆናቸው ትውልድ ተሻጋሪ እንዳይሆኑ አድርጓቸዋል፡፡
እነዚህን ችግሮች ለመፍታትና በአግባቡ ለመጠበቅ እንዲቻል ባቀረቡት የመፍትሔ ሃሳብ ደረጃውን የጠበቀና ተስማሚ በሆነ ቦታ ማኖር፤ ቴክኖሎጂን መጠቀም፤ ስለ አጠቃቀሙ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን መሥራት፤ የማይክሮ ፊልም ዲጂታል ቴክኖሎጂን መጠቀም፤ በጉብኝት ወቅት በእጅ እንዳይነካኩ ጥረት ማድረግ የሚሉትን እንደመፍትሔ አቅርበዋል፡፡
ሦስተኛው በአቶ ዮሴፍ ደምሴ የቀረበው “ቅርሶችን መለየትና መመዝገብ” በሚለው ጥናታዊ ጽሑፋቸው የአንድ አገር የባሕል፤ የታሪክ እንዲሁም የማንነት መገለጫ ከሆኑ ዋና ዋና ነገሮች አንዱ የጽሑፍ ሀብት እንደሆነ ጠቅስዋል፡፡
አንድ የሥነ ጽሑፍ ሀብት ቅርስ ነው የሚባለው የመረጃ ምንጩ ያለው የመረጃ ዋጋ፤ የመረጃ ምንጩ ታሪካዊ ዋጋ፤ የመረጃ ምንጩ በቀላሉ ያለመገኘት፤ የተጻፈበት ዘመን መቆየት፤ የተለየ የአጻጻፍ ስልት መከተሉ ቅርስ ሊያሰኘው እንደሚችል አብራርተዋል፡፡
የሥነ ጽሑፍ ሀብቶቹን መመዝገብ ያለውን ጠቀሜታ ሲገልጹም ቅርሶቹ በሚገኙባቸው ቦታዎች አስፈላጊውን የመለየትና የመመዝገብ ሥርዓት በአገር አቀፍ ደረጃ ወጥ በሆነ መንገድ ዓይነታቸውንና ቁጥራቸውን ለመለየት ያስችላል ብለዋል፡፡
የመምረጫ መስፈርቶቹንም ሲተነትኑ እውነተኛነቱ፤ የተለየና ሊተካ የማችል መሆኑ፤ ጊዜውን፤ ቦታውን፤ ርእሰ ጉዳዩን፤ የተለየ የአጻጻፍ ስልት መከተሉን፤ ዓለማቀፋዊ ፋይዳነቱ በዋነኛነት ሊመዘን እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ከታዳሚዎች በተሰጡ አስተያየቶችም ተቀናጅቶ መሥራት ያለመቻሉ ትኩረት ከተሰጣቸውና ሰፋ ያለ ውይይት ከተደረገባቸው ሃሳቦች አንዱ ነው፡፡ ባለ ድርሻ አካላት በግል የሚያደርጓቸው ጥረቶች ብቻ ውጤታማ ሥራ መሥራት እንዳላስቻለ፤ የባለሙያ እጥረት መኖሩን፤ በተለይም በዘርፉ ተመርቀው የሚወጡ ባለሙያዎች በሚፈለግባቸው የሥራ ዘርፍ አለመመደብ፤ የአመለካከት ችግር በስፋት መታየቱ፤ ዕውቀትን የመደበቅ ችግር፤ ጥንታዊያን መዛግብት የሚጠበቁበት፤ የሚመዘገቡበትና የሚሰራጩበት ፖሊሲ ያለመኖር፤ በየደረጃው የሚገኙ የመንግሥት አካላት በቂ ግንዛቤ ያለመኖርና የማስፈጸም ፍላጎታቻው አናሳ መሆን፤ የሚመለከታቸው አካላት ቁርጠኝነት ማነስ፤ ሞክሼ ፊደላት አባቶቻችን የተጠቀሙት አስፈላጊና ምክንያታዊ በሆነ መንገድ አስበውበት ያደረጉት በመሆኑ ለመቀነስ የሚደረገው እንቅስቃሴ ቤተ ክርስቲያንም ሆነች ሀገራችን ያሏትን ቅርሶች እንደማውደም ስለ መቆጠሩ እንደ መሠረታዊ ችግሮች ተነስተዋል፡፡
ጥናት አቅራቢዎቹ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሾቻቸውን የሰጡ ሲሆን፤ የኤጀንሲው ዋና ዳሬክተር አቶ አብርሃም ጮሻ ማጠቃለያ ሃሳባቸውን አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከባለ ድርሻ አካላት ጋር የሚደረገው ግንኙነት የጠነከረና ሓላፊነትና ተጠያቂነትን በማስፈን መስመር ማስያዝ፤ ጥናት የሚያደርጉ ምሁራንን ከገዳማትና ከተቋማት ጋር ማቀናጀት፤ ለሥነ ጽሑፍ ሃብቶቻችን ሃገራዊ መቆርቆርን መፍጠር፤ በስጦታም ሆነ በግዢ ቅርሶቹን ለማሰባሰብ ኤጀንሲው ጥረት በማድረግ ላይ መሆኑን፤ የተማረውን የሰው ኃል በተገቢው ቦታ ገብተው አገራዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ማድረግ፤ የፖለቲካ ተጠሪዎች፤ የተቋማት ተጠሪዎችና ተቋሙ፤ እንዲሁም ማኅበረሰቡ ላይ የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ መሥራት፤ የሞክሼ ፊደላትን በተመለከተ መንግሥት ያሳለፈው ውሳኔና አቅጣጫ የሰጠበት ሁኔታ የሌለ በመሆኑ ውሳኔውን ካሳለፈው አካል ጋር ግንኙነት መፍጠርና መፍትሔ መሻት፤ ውጪ ያሉ የሥነ ጽሑፍ ቅርሶችን ለማስመለስ ኮሚቴ ተዋቅሮ አቅጣጫ ለማስያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ከውይይቱ በኋላ በኤጀንሲው ውስጥ አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ ዋና ዋና የሥነ ጽሑፍ ክምችት ክፍሎች በታዳሚዎች ተጎብኝተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ በ1936 ዓ.ም. በቀዳማዊ ዐፄ ኃይለ ሥላሴ “የሕዝብ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር” ተብሎ የተመረቀ ሲሆን፤ 300 የብራና መጻሕፍትን በመለገስ አገልግሎት የጀመረ ተቋም ነው፡፡
Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1641-2014-12-11-19-24-10