አምስት የቅዱሳን መዲና የሆኑ ገዳማትን ለመደገፍ ውይይት ተካሄደ
- Details
- Created on Thursday, 20 November 2014 01:38
- Written by ቀዳሚ ገጽ
መ/ር ሳሙኤል ተስፋዬ
ኅዳር 12 ቀን 2007 ዓ.ም.
በሰሜን ሸዋ ሀገረ ስብከት አምስቱ የቅዱሳን መዲናዎች በመባል የሚታወቁት ገዳማት በተለይ ከ1950ዎቹ ጀምሮ ቅዱሳኑ በቤተ ክርስቲያን ለምእመናን እየተገለጡ፤ ድምጽ እያሰሙ፣ ያስተምሩ፣ ይገስጹ፣ ይመክሩ፣ መጻዒውን ያመለክቱ እንደነበር ኅዳር 8 ቀን 2007 ዓ.ም በደብረ መንክራት ሚጣቅ ቅዱስ አማኑኤል ገዳም ገዳማቱን ለመርዳት በተደረገው የምክክር ውይይት ለመረዳት ተችሏል፡፡
ቅዱሳኑ በመገለጥ መልእክቶቻቸውን ያስተላልፉባቸው የነበሩ ገዳማት “የቀደመ ክብራቸው እንዳይጠፋና የአብነት ት/ቤቶችን ለማጠናከር በልማት ሥራዎች እንደግፍ::” በሚል መሪ ቃል በዘንባባ ደብረ ቢዘን መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ ገዳም አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ሁለት ማኅበራት አስተባባሪነት ከአምስቱ ገዳማት የመጡ አባቶች፣ ገዳሙን በቅርብም በሩቅም ሆነው የሚረዱ ምእመናንና የማኅበራቱ አባላት በመሆን ውይይት ተካሂዷል::
ውይይቱ በጥናት ተደግፎ ለገዳማቱ ድጋፍ ለማድረግ ቀጠሮ የተያዘ ሲሆን ምእመናን የእግዚአብሔርን ቸርነት የቅዱሳንን ተጋድሎ በመረዳታቸው በቀጣይ ገዳማቱን ለመርዳትና ከቅዱሳኑ በረከት ለማግኘት በርካታ ምእመናን ተነሳሽነታቸውን አሳይተዋል ፡፡
አምስቱ የቅዱሳን መናኸሪያ ገዳማት ስምና ከደብረ ብርሃን ከተማ ያላቸው ርቀት
1. ደብረ መንክራት ሚጣቅ ቅዱስ አማኑኤል ገዳም ከደብረ ብርሃን ከተማ በአንኮበር መንገድ 34 ኪ.ሜ
2. ቦለድ ባለወልድ ከደብረ ብርሃን ከተማ በአንኮበር መንገድ 45 ኪ.ሜ
3. ዘንባባ ደብረ ቢዘን ቅዱስ ዮሐንስ ገዳም ከደብረ ብርሃን በኩክየለሽ መንገድ 24 ኪ.ሜ ሲሆን 16 ኪ.ሜ መኪና መንገድ አለው፡፡
4. በለስ ዋሻ ናዝራዊ ኢየሱስ ገዳም ከደብረ ብርሃን ከተማ በቀይት ወርቄ መንገድ 43 ኪ.ሜ እና የ45 ደቂቃ የእግር መንገድ ወይም ከዘንባባ ደብረ ቢዘን ቅዱስ ዮሐንስ ገዳም የ2፡00 ሰዓት የእግር ጉዞ
5. አንጉይ ሕርያቆስ ቅድስት ማርያም ገዳም ከደብረ ብርሃን እነዋሪ መንገድ 45 ኪ.ሜ የ1 ሰዓት የእግር ጉዞ
በውይይቱ መርሐ ግብሩ ወቅት ለአምስቱ ገዳማት ብርድ ልብስ፣ ጧፍ፣ እጣን፣ ዘቢብ፣ ለአባቶችም ካባ የተሰጠ ሲሆን በዕለቱ ለደብረ መንክራት ሚጣቅ አማኑኤል አብነት ት/ቤት ማጠናከሪያ የሚውል ከ20 ሺህ ብር በላይ እርዳታ ተደርጓል፡፡
የአምስቱን ገዳማት ታሪክ ወደፊት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እናቀርባለን፡፡
የቅዱሳኑ በረከት አይለየን
Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1609--1950-8-2007-