“ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፤ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥሁት ሥፍራ አመጣቸዋለሁ” /መጽ.ነህ.1፤9/

 ጥቅምት 28 ቀን 2007 ዓ.ም.

በእንዳለ ደምስስ

  •  “በአንድ ወቅት ክርስትና ለማስነሳት ሌሊት ወደ ገፈርሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ስንሔድ የጅብ መንጋ መጥቶ ክርስትና የሚነሳውን ሕጻን በልቶብናል /የገፈርሳ ጉቼ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ በዓለ ወልድ አባ ኪሮስ ወአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቤተ ክርስቲያን አጥቢያ ምእመናን/


gefersa1 በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት በገፈርሳ ወረዳ ጉቼ ቀበሌ ከአዲስ አበባ ታጠቅን አልፎ ወደ ሆለታ በሚስደው መንገድ የሚገኙ ምእመናን ለረጅም ዘመናት ቤተ ክርስቲያን ሳይኖራቸው እዚህ ዘመን ላይ ደርሰዋል፡፡ በአቅራቢያቸውም ሥርዓተ አምልኮ የሚፈጽሙበት፤ ልጆች ቢወልዱ ክርስትና የሚያስነሱበት፤ ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩ የሚቀበሩበት ቤተ ክርስቲያን አልነበራቸውም፡፡

ማንኛውንም አገልግሎት ለማግኘት ወደ ገፈርሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ለመሄድ ከዐሥር ኪሎ ሜትር በላይ መጓዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ወደ ገፈርሳ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ወይም ደግሞ መናገሻ አምባ ማርያም ከስምንት ኪሎ ሜትር በላይ ለመጓዝም ይገደዳሉ፡፡ በአንድ ወቅት ክርስትና ለማስነሳት ሌሊት ወደ ገፈርሳ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ሲሄዱ ጅብ መጥቶ ክርስትና የሚነሳውን ሕጻን እንደበላባቸውም ከአካባቢው ምዕመናን ይነገራል፡፡


በዚህ ላይ በአካባቢው የሌሎች እምነት ተከታዮች ተጽእኖ፤ የነዋሪዎቹ በባእድ አምልኮ ውስጥ መግባት፤ በተለይም ልጆች ከተወለዱ በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያን ከመውሰድ ይልቅ የተለያዩ የባእድ አምልኮ ተግባራት ይፈጽማሉ፡፡


“በአቅራቢያችን ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ ልጆቻችንን ክርስትና የምናስነሳው በእግር መሄድ ሲጀምሩ ነው፡፡ ከተሳካልንም ዓመት ጠብቀን የጥምቀት ክብረ በዓል ላይ ነው፡፡ የሚያስተምረን የለም፤ እኛም ወገኖቻችንም ተቸግረናል” በማለት የአጥቢያው ምእመናን ሀዘናቸውን ሲገልጹ መስማት የተለመደ ነው፡፡ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሁኔታው ያሳሰባቸውና በአካባቢው ቤተ ክርስቲያን ባለመኖሩ በመንፈሳዊ ቅናት የተቃጠሉ፤ ለእምነታቸው የሚቆረቆሩ፤ ምእመናን ደግሞ ለምን ተሰባስበን ቤተ ክርስቲያን አንሰራም በማለት ይነጋገራሉ፡፡


እስከ መቼ ከቤተ ክርስቲያንና ከእምነታችን ርቀን እንኖራለን? በማለት ሦስት ሆነው ቤተ ክርስቲያን መትከል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ በመወያየት በባእድ አምልኮ ተዘፍቀው የሚገኙትን ወገኖቻቸውን ወደ ቤተ ክርስቲያን ለመመለስ፤ ወደ ሌላ እምነት ተቋማት የተወሰዱትንም ለማስመለስ በጸሎት በመጽናት ሥራዎችን ለመሥራት ይስማማሉ፡፡ ሦስት ሆነው በአንድ ከብቶች ማደሪያ መጋዘን ውስጥ ተሰባስበው ጠዋትና ማታ ጸሎት ማድረግ ይጀምራሉ፡፡ ቁጥራቸውም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተበራከተ መጥቶ 21 ደረሰ፡፡ የግለሰቦቹ ለእምነታቸው ያላቸውን ጥንካሬ በመመልከት ከአቅራቢያው ከሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት በአገልግሎት ላይ የሚገኙ አባቶች ጠዋትና ማታ እየመጡ በጸሎት እያገዟቸው፤ ሌሊት ኪዳን እያደረሱ ጸሎታቸውን ይቀጥላሉ፡፡


በድንገት ግን የምእመናኑን ጥረት የሚያጨናግፍ አንድ ክስተት ተፈጠረ፡፡ “ማን ፈቅዶላችሁ ነው በዚህ ቦታ ተሰባስባችሁ ጸሎት እንድትጸልዩ የፈቀደላችሁ?” በሚል ከመጋዘኑ እንዲወጡ ተደረጉ፡፡ በተደጋጋሚ በጉዳዩ ላይ ክርክር ቢያነሱም የተወሰኑ ምእመናን ለእሥር ተዳረጉ፡፡ ጥረታቸው ግን ቀጠለ፡፡ ሌላ ቦታ ለማግኘት ያደረጉትም እንቅስቃሴ ውጤት ሳያመጣ ቀረ፡፡


gefersa3 እግዚአብሔርን በንጹሕ ልቦና ለሚፈልጉት ቅርብ ነውና “በቃሌ ወደ እግዚአብሔር ጮኽሁ፤ ከተቀደሰ ተራራውም ሰማኝ” መዝ. 3፤4 እንዲል ቅዱስ ዳዊት በጭንቀት ውስጥ ባሉበት ወቅት፤ እግዚአብሔር ከመካከላቸው አንድ ሰው አስነሳ፡፡ አቶ ደቻሳ ድሪባ ከምእመናኑ አንዱ ሆኖ አብሮ ሲጨነቅ ነበርና አንድ ውሳኔ ይወስናል፡፡ “ወደፊት እግዚአብሔር የሚያደርገውን አናውቅምና ኑ የእኔ እርሻ ቦታ ላይ ላስቲክ ወጥረን እንጸልይ” በማለት ፈቀደ፡፡ ለመከር የተቃረበውን የስንዴ ማሳ ሳይደርስ በማጨድ ለጸሎት ቦታ ተዘጋጀ፡፡ “የቤትህ ቅናት አቃጠለኝን” ይሉ እንደነበር ቅዱሳን ላስቲክ ተወጥሮ ጸሎታቸውን ቀጠሉ፡፡የእግዚአብሔር ፈቃድ ሆነና ዕለት ዕለት በርካታ ምእመናን ይመጡ ጀመር፡፡


ግንቦት 29 ቀን 2005 ዓ.ም. በአንድነት ጸሎት ተጀምሮ ለቀበሌ፤ ለወረዳ ቤተ ክህነት፤ ለሀገረ ስብከት በማሳወቅ፤ በተጨማሪም ለቡራዩ ከተማ አስተዳደር “እኛም ቤተ ክርስቲያን በአጥቢያችን ያስፈልገናል” በማለት በአጥቢያው በቅርበት ያሉትን የስድስት ጎጥ ምእመናንን ፊርማ በማሰባሰብ የቦታ ጥያቄ አቀረቡ፡፡ መሥራች ኮሚቴም አቋቋሙ፡፡


የምእመናኑን ጥያቄ በመረዳት የወረዳው ቤተ ክህነት ሥራ አስኪያጅ ላስቲክ ወጥረው የሚጸልዩበት ቦታ ድረስ በመምጣት የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስና የሀገረ ስብከቱ ሠራተኞች፣ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ተወካዮች አማካይነት ቤተ ክርስቲያን እንዲሰሩ ተፈቀደላቸው፡፡ የቦታው ባለ ይዞታም አቶ ደቻሳ ድሪባ ሰባት ቤተሰባቸውን የሚያስተዳድሩበትን የእርሻ ቦታ “የአካባቢው ነዋሪ እንደሚያውቀው፤ ያለችኝ መሬት ይችው ናት፡፡እግዚአብሔርን የምናመልክበት የቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ችግር ይፈታ እንጂ እኔም ሆንኩ ንብረቴ የእግዚአብሔር ነን፤ ለሃይማኖቴ ካለኝ ቅናት የተነሳ ለምእመናን እንባ ማበሻ ይሆን ዘንድ ያለኝን ነው የሰጠሁት” በማለት ያላቸውን 2500 ካሬ ሜትር የእርሻ ቦታ ሰጡ፡፡ ኮሚቴውም ውሎ ሳያድር ሥራውን ጀመረ፡፡ መቃኞውንም በምእመናን ተሳትፎ በአጭር ጊዜ ውስጥ ተሠርቶ ተጠናቀቀ፡፡


ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምእራብ ሸዋ ሀገረ ስበከት ሊቀ ጳጳስ የመቃረቢያው ቤተክርስቲያን መሠራት ካረጋገጡ በኋላ በምእመናኑ ምርጫ መሠረት የበዓለ ወልድ ታቦት እንዲገባ ፈቀዱ፡፡ በተጨማሪነትም ብፁዕነታቸው ሌሎች ታቦታት መኖር አለባቸው በማለታቸው የአቡነ ኪሮስ እና የአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ታቦታት እንዲገቡ አደረጉ፡፡ ሐምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም. ቅዳሴ ቤቱ በድምቀት ተከበረ፡፡ የገፈርሳ ጉቼ ምእመናን የቤተ ክርስቲያን ናፍቆትና ምኞት ተሳካ፡፡ የገፈርሳ ጉቼ መካነ ቅዱሳን ቅዱስ በዓለ ወልድ አባ ኪሮስ ወአባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት መሥጠት ጀመረ፡፡


በአጥቢያው የባእድ አምልኮ መመናመን፡-

gefersa2 ቤተ ክርስቲያኑ ከተተከለበት ጊዜ ጀምሮ በባእድ አምልኮ ተይዘው፤ ራሳቸውን ከእግዚአብሔር ለይተው የነበሩ ምእመናን ወደ ቤተ ክርስቲያን በመምጣት ያመለኩባቸው የነበሩ እቃዎችን አምጥተው በማስረከብ ወደ ቀደመው እምነታቸው ሲመለሱ መመልከት የተለመደ ሆነ፡፡ ወላጆች የወለዷቸውን ሕፃናት በአርባና በሰማንያ ቀናቸው ክርስትና ለማስነሳት በቁ፡፡ ወደ ሌላ እምነት ተወስደው የነበሩ ምእመናንም ወደ እናት ቤተ ክርስቲያን በመመለስ ላይ ይገኛሉ፡፡


ጸበል፡-

የቦታው ባለ ይዞታ አቶ ደቻሳ ድሪባ ታታሪ ሠራተኛ በመሆናቸው፤ ስምንት ሜትር ጥልቀት ያለው ጉድጓድ በመቆፈር በውኃ መሳቢያ ፓምፕ እየታገዙ በዓመት ሁለት ጊዜ አትክልት እያመረቱ ልጆቻቸውን ያሳድጉበት የነበረ ነው፡፡ መቃኞው ሲሰራም ለግንባታ የሚያስፈልገውን ውኃ የተጠቀሙበት ከዚሁ ጉድጓድ ነው፡፡ ነገር ግን እግዚአብሔር ባወቀ ይህ የጉድጓድ ወኃ ጸበል በመሆኑ፤ በርካታ ሕሙማን እየጠጡትና እየተረጩት ከሥጋ ደዌ ይፈወሱ ስለነበር ተባርኮ በጸበልነት ምእመናን እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡ በርካታ ሕሙማን ተፈውሰው ምሥክርነት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡

 

መሥራች ኮሚቴው ያጋጠመው ችግር፡-

ምእመናን ለእምነታቸው በመቆርቆር በአቅራቢያቸው ቤተ ክርስቲያን ለመትከል ከነበራቸው ምኞትና ጉጉት የተነሳ ሌት ከቀን በጸሎት በመጠመድ፤ የሚደርስባቸውን ጫና ሁሉ በመቋቋም እግዚአብሔር ፈቃዱ ሆኖ ቤተ ክርስቲያኑን በመትከል ያሰቡት ተሳክቷል፡፡ ነገር ግን መሥራች ኮሚቴው አንድ ትልቅ ችግር አጋጥሞታል፡፡ ቤተ ክርስቲያኑ እንዲሠራ፤ ከ2500 ካሬ ሜትር በላይ የሆነውን የእርሻ ሥፍራ ለእግዚአብሔር አገልግሎት እንዲውል የሰጡት አቶ ደቻሳ ያለ ምንም መተዳደሪያ መቅረታቸው እረፍት ነሣቸው፡፡


“ግለሰቡ ቦታውን ሲሰጡን ለእምነታቸው ካላቸው መንፈሳዊ ቅናት የተነሳ በአጥቢያው ቤተ ክርስቲያን እንዲኖር ከመመኘት ነው፡፡ አንድ ዓይናቸውን አጥፍተው ነው የሰጡን፤ ሌላ የእርሻ ቦታ የላቸውም፤ ቦታው ዙሪያው የተተከሉ አጸዶችና ሁለት ክፍል ቤት ጭምር ለእግዚአብሔር አሳልፈው ያላቸውን ነው የሰጡን፡፡ እኛ ማደሪያ ሥፍራችንን አደላድለን እየበላንና እየጠጣን፤ እሳቸው ግን ከነቤተሰቦቻቸው ጾማቸውን እያደሩ ነው፡፡ ምትክ ወይም በገንዘብ ተገምቶ ለመሥጠት ስምምነት ላይ ብንደርስም እኛም ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ ላይ ስለምንገኝ አቅም አነሰን፡፡ የበጎ አድራጊ ምእመናን ድጋፍ እንሻለን” በማለት የመሥራች ኮሚቴ አባላት ጭንቀታቸውን ይገልጻሉ፡፡


“ወደ እኔ ብትመለሱ ግን ትእዛዜንም ብትጠብቁ፤ ብታደርጓትም ምንም ከእናንተ ሰዎች እስከ ሰማይ ዳርቻ ቢበተኑ ከዚያ እሰበስባቸዋለሁ፤ ስሜም ይኖርበት ዘንድ ወደ መረጥኩት ስፍራ አመጣቸዋለሁ፡፡” / ነህ.1፤9/ እንዲል ነብዩ ነህምያ የእግዚአብሔር ጊዜ ሲደርስ በባእድ አምልኮ ተጠልፈው የነበሩትን ከርኩሰትና ከክፉ ግብራቸው ተመልሰው፤ ከተጠለሉባት እናት ቤተ ክርስቲያናቸው አፈንግጠው ወደ ሌሎች የእምነት ተቋማት ኮብልለው የነበሩትን ደግሞ ወደ ቀደመችው ርስታቸው ወደ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እግዚአብሔር እየሰበሰባቸው ነው፡፡ የተሰበሰቡት እንዳይበተኑ ችግራቸውን በመጋራት ልናጠናክራቸው ይገባል፡፡ 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/--mainmenu-43/1599--19