በዓለ ሲመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል

ዲ/ን ሽመልስ መርጊያ

ህዳር 8/2007 ዓ.ም

 

የሰው ልጅ በገነት እንደ ቅዱሳን መላእክት በቅድስና አምላኩን በማመስገን በደስታ ይኖር ነበር፡፡ ነገር ግን “ክፉና ደጉን ከምታሳውቀው ዕፀ በለስ እንዳትበላ” ተብሎ የተሰጠውን ትእዛዝ በመተላለፉ ምክንያት ከአምላኩ ተለየ(ዘፍ.3፡6)፡፡እግዚአብሔር በአርአያውና በአምሳሉ የፈጠረው ሰው ክብሩን አጣ፣ ጸጋው ተገፈፈ፣ ፈጣሪውንም አሳዘነ፡፡ ቅዱሳን መላእክትም በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረው ሰው ከክብሩ ተዋርዶ ሲመለከቱ ተከዙ፡፡

 

የሰው ልጅ ጠፍቶ እንዲቀር ያልወደደው እግዚአብሔር ወልድ ሰውን ለማዳን ራሱን ዝቅ አድርጎ ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሱዋ ነፍስ ነስቶ ተወለደ፡፡ቅዱሳን መላእክትም ከላይ ከአርያም ከአባቱ ሳይለይ እግዚአብሔር ወልድ ሰውን ለማዳን ሲል በግዕዘ ሕፃናት ተወልዶ፣ በእናቱም እቅፍ ሆኖ፤ እንስሳት እስትንፋሳቸውን እያሟሟቁት በማየታቸው ተደነቁ፡፡ ሰውን ለማዳን ሲል ራሱን ዝቅ በማድረግ የባርያውን አርአያ እንደነሣ አስተውለው “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት፣ ወሰላም በምድር ሥምረቱ ለሰብእ” (ሉቃ.2፡14) ብለው አመሰገኑት፡፡

ጌታችንም በመስቀሉ የማዳን ሥራውን ሲፈጽም ተጎሳቁሎ የነበረውን የሰው ባሕርይ ወደ ቀድሞ ክብሩ መለሰው፡፡ ስለዚህም እንደ ቅዱሳን መላእክት አምላኩን ለማመስገን እድሉን አገኘ፡፡ (ዮሐ.4፡23)  ነገር ግን ከእነርሱ ጋር በመሆን  ሙሉ ለሙሉ በምስጋና  የሚሳተፈው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ሙታንስ በሚነሡበት ጊዜ በሰማያት እንደ እግዚአብሔር መልአክት ሆነው ይኖራሉ…….” (ማቴ.22፡30) እንዳለው  በትንሣኤ ዘጉባኤ ነው፡፡ እስከዚያ ድረስ ግን በዚህ ምድር ሳለን ከእኛ የሚጠበቅብንን ፣ ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቃል ያስተማረንን፣ በሥራም ያሳየንን ተግባር ተግብረን፣ እንደ ቅዱሳን መላእክት ለአምላካችን በመንፈስና በእውነት በመሆን አምልኮታችንን እንድንፈጽም የእነርሱ ተራዳኢነት በእጅጉ ያስፈልገናል፡፡ ስለዚህም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “መላእክት ሁሉ መናፍስት አይደሉም? የዘለዓለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ ስለ አላቸው ሰዎችስ ለአገልግሎት ይላኩ የለምን?” (ዕብ.1፡14) ማለቱ፡፡ “የዘለዓለም ሕይወትን ይወርሱ ዘንድ” የተባልነው ጌታችን መድኅኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በወንጌሉ “እነርሱ በእውነት ቅዱሳን ይሆኑ ዘንድ ስለእነርሱ ራሴን እቀድሳለሁ፡፡ የምለምንህም ስለ እነዚህ ብቻ አይደለም፤ በቃላቸው ስለሚያምኑብኝ ሁሉ ነው እንጂ” (ዮሐ.17፡19-20)እንዳለው በክርስቶስ አምነን ለተጠመቅነው ክርስቲያኖች ነው፡፡

 

mikeale እናት ልጁዋን እንድትንከባከብና እንድታገለግል ሁሉ ቅዱሳን መላእክትም የዘለዓለም ሕይወትን እንድንወርስ ይራዱናል፡፡ (ሉቃ.13፡6-9) ያለ እነርሱ እርዳታና ድጋፍ በቅድስና ሕይወት አድገን የመንግሥቱ ወራሾች መሆን አይቻለንም፡፡ እንዲህም በመሆኑ በመንፈስ ቅዱስ የልጅነት ጸጋን ከማግኘታችን በተጨማሪ ቅዱሳን መላእክት እኛን ይራዱን ዘንድ ጠባቂ ተደርገው ተሰጥተውናል፡፡ (ማቴ.18፡10)

 

ቅዱስ ጳውሎስ “እናንተ ግን የሕያው እግዚአብሔር ከተማ ወደምትሆን ወደ ጽዮን ተራራ በሰማያት ወደ አለችው ኢየሩሳሌም ደስ ብሎአቸው ወደሚኖሩ አእላፍ መላእክትም ደርሳችኋል” (ዕብ.12፡22) በማለት እንደተናገረው በክርስቶስ የማዳን ሥራ ከቅዱሳን መላእክት ጋር አንድ ቤተሰብ መሆንን አግኝተናል፡፡ ስለዚህም ጉዞአችንን ጨርሰን ገድላችንን ፈጸመን ለክብር እንድንበቃ ይራዱናል፡፡ በመሆኑም የእኛ ሕይወት በኃጢአት ውስጥ መገኘት ሲያሳዝናቸው፣ በንስሐ ወደ አባታችን መመለሳችን ደግሞ በእጅጉ ያስደስታቸዋል፡፡ (ሉቃ.15፡7) ስለዚህ ስለእኛ በቅድስና ሕይወት ይተጋሉ፡፡ቅዱስ ጳውሎስ "ለራሱ ስለ ሆኑት፥ ይልቁንም ስለ ቤተ ሰዎቹ የማያስብ፥ ማንም ቢሆን ሃይማኖቱን የካደ፥ ከማያምንም ይልቅ የከፋ ነው" ይላል፡፡ (1ጢሞ.5፡8) ስለዚህ እኛ የእነርሱ ቤተሰብ ሆነናልና ቤተሰባዊ ግዴታቸውን ለመወጣት ሲሉ፣ ደካማው ብርቱን እንዲረዳ ቅዱሳን መላእክትም እኛን ለመርዳት ይተጋሉ፡፡ ነገር ግን የእነርሱ እርዳታ ለእኛ የሚፈጸምልን ተራዳኢነታቸውንና ምክራቸውን የተቀበልን እንደሆን ብቻ ነው፡፡ ምክንያቱም እነርሱም እንደ አምላካቸው በእኛ ነጻ ፈቃድ ውስጥ ጣልቃ አይገቡምና፡፡ እንዲህም ስለሆነ የሎጥ ሚስት ምንም እንኳ በመልአኩ እጅ ብትያዝም ለመልአኩ ቃል ባለመታዘዙዋና ለመዳን ባለመፍቀዱዋ የጨው ሐውልት ሆና ቀርታለች (ዘፍ.19፡26)፡፡ በእርግጥ ቅዱስ ጳውሎስ  “በመላእክት የተነገረው ቃል ጽኑ ከሆነ መተላለፍና አለመታዘዝ የጽድቅን ብድራት ከተቀበለ..” (ዕብ.2፡2) በማለት እንደገለጠልን  እግዚአብሔር ለላከው መልአክ አለመታዘዝ ታላቅ የሆነ ቅጣትን ማምጣቱ የማይቀር ነው፡፡ ስለዚህም ቤተ ክርስቲያን ልጆቹዋ የመላእክትን ተራዳኢነት አውቀው እንዲጠቀሙና የመንግሥቱ ወራሾች ለመሆን እንዲበቁ ስትል ለቅዱሳን መላእክት የመታሰቢያ ቀን በመስጠት በእነርሱ የምናገኛቸውን እርዳታዎች እንዲታወሱ ታደርጋለች፡፡

 

በዚህም መሠረት በህዳር ወር በዐሥራ ሁለተኛው ቀን ቤተ ክርስቲያናችን የታላቁ መልአክ የቅዱስ ሚካኤልን በዓለ ሲመት በታላቅ ድምቀት  ታከብረዋለች፡፡ እንደ ቅዱሳን አባቶቻችን አስተምህሮ ዳር 12 ቀን ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል በኢዮር ባለችው በአራተኛይቷ ከተማ በሚኖሩት ኃይላት እና በአሥሩ ነገደ መላእክት ላይ አለቃ ሆኖ የተሾመበት ቀን ነው፡፡እግዚአብሔር ሳጥናኤልን በትዕቢቱ ምክንያት ከሥልጣኑ ገፍፎ ወደ ምድር ሲጥለው ቅዱስ ሚካኤል በእርሱ ቦታ በዐሥሩ ከተማ በመቶውም ነገደ መላእክት ላይ ተሹሟል፡፡(ይህን ሁለተኛውን ሹመት ያገኘው በሚያዚያ 2  እንደሆነ አክሲማሮስ በሚባለው የቤተክርስቲያናችን መጽሐፍ ላይ ሰፍሮ አናገኛለን፡፡)

 

የቅዱስ ሚካኤል ሹመት በነገደ መላእክት ላይ ብቻ ግን አይደለም ፤ ነገር ግን የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆኑት ላይም ጭምር ነው ፡፡ ይህም እንደሆነ እንድንረዳ በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝብ የተባለውን እስራኤል ዘሥጋን ሲራዳና ሲጠብቅ እንደነበረ ተጽፎልን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ መጽሐፍ ቅዱስ መልአኩ ቅዱስ ሚካኤል ለኢያሱ በኢያሪኮ ምድረ በዳ እንደተገለጠለት “… ዐይኑን አንሥቶ ተመለከተ እነሆም የተመዘዘ ሰይፍ የያዘ ሰው በፊቱ ቆመ፤ ኢያሱም ወደ እርሱ ቀርቦ “ከእኛ ወገን ወይስ ከጠላቶቻችን ወገን ነህ? አለው፡፡ እርሱም “እኔ የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ሆኜ አሁንም ወደ አንተ መጥቼአለሁ” (ኢያ.5፡13) ይለናል፡፡

 

st.mickeale

እግዚአብሔር አምላክ ሕዝበ እስራኤልን ከግብጽ ባርነት ነፃ ሲያወጣቸው ይመራቸው የነበረ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ነበር፡፡ ሹመቱ በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይም በመሆኑ ስለ እነርሱ ዲያብሎስ ይዋጋው፣ በጸሎትም ይራዳቸው ነበር፡፡ ነገር ግን ኃጢአት ሠርተው ሲያገኛቸው ለእግዚአብሔር አድልቶ ኃጢአተኞችን ስለሚቀጣ እግዚአብሔር ሕዝቡን “በፊቱ ተጠንቀቁ ቃሉንም አድምጡ ስሜም በእርሱ ስለሆነ ኃጢአት ብትሠሩ ይቅር አይልምና አታስመርሩት” (ዘጸ.23፡21)ብሎ አስጠንቅቋቸው ነበር፡፡ ይህም ቅዱስ ሚካኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙን ያስረዳናል፡፡ ነገር ግን ከላይ የተጠቀሱት ጥቅሶች ሕዝበ እስራኤልን ይራዳቸው የነበረው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ አያረጋግጥም የሚል ካለ “መልአክ” የተባለው ቅዱስ ሚካኤል ስለመሆኑ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ነቢዩ ዳንኤል በተላከ ጊዜ ገልጦልን እናገኛለን፡- ቅዱስ ገብርኤል በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ቅዱስ ሚካኤል ስለመሾሙ ሲመሰክር “በእውነት በመጽሐፍ የተጻፈውን እነግርሃለሁ፤ በዚህም ነገር ከአለቃችሁ ከሚካኤል በቀር የሚረዳኝ ማንም የለም”(ዳን.10፡21)ብሎአል፡፡ ስለዚህም ለኢያሱ የተገለጠውና እስራኤላውያንንም የመራው መልአክ ቅዱስ ሚካኤል መሆኑን እንረዳለን፡፡

 

የቅዱስ ሚካኤል አለቅነት በሐዲስ ኪዳንም አንደሚቀጥል ይህ ነቢይ በትንቢቱ “በዚያ ዘመን ስለ ሕዝብህ ልጆች የሚቆመው ታላቁ ሚካኤል ይነሣል..” (ዳን.12፡1) በማለት ተናግሮለታል፡፡ ስለዚህም ቅዱስ ሚካኤል እኛን ከሰይጣን አሽክላና ወጥመድ ይጠብቀንና በጸሎቱ በእግዚአብሔር ፊት ይቆምልን ዘንድ በእኛም ላይ ሹም ነው፡፡ ምክንያቱም እኛ የእግዚአብሔር ሕዝቦችና የርስቱ ወራሾች ነንና፡፡

 

እግዚአብሔር ነቢዩ ሙሴን የሕዝቡ መሪ አድርጎ መሾሙ እጅግ ትሑትና ስለመንጎቹ ነፍሱን እንኳ አሳልፎ እስከመስጠት ደርሶ ስለሚወዳቸው ነበር፡፡(ዘኁል.12፡3፤ዘጸአ.32፡32) በሕዝቡም ላይ እርሱን መሾሙ እንዲሠለጥንባቸው ወይም እንዲገዛቸው ሳይሆን በትምህርቱና በጸሎቱ እነርሱን እንዲቤዣቸው ነው፡፡ እንዲህም ስለሆነ ቅዱስ እስጢፋኖስ ስለሙሴ ሲመሰክር “እግዚአብሔር ሹምና ቤዛ አድርጎ ላከው”አለ፡፡ (የሐዋ.7፡35) እንዲሁ ቅዱስ ሚካኤል ነው፡፡ ቅዱስ ሚካኤል እጅግ ትሑትና ለሠራዊቱ ተቆርቋሪ የሆነ መልአክ በመሆኑ በመላእክትና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ተሾመ፡፡ በመላእክትና በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ መሾሙ  ልክ እንደ ሙሴ በእነርሱ ላይ ሊሠለጥንባቸው ወይም ሊገዛቸው ሳይሆን መላእክትን ሊመራ ፣ እኛን ደግሞ ከሰይጣን ጥቃት ሊጠብቀንና በጸሎቱ ሊራዳን ነው (ይሁዳ.12) ፡፡

 

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ቅዱሳን መላእክት እኛን እንደሚጠብቁና እንደሚራዱ እንዲሁም ስለእኛ በፊቱ አንደሚቆሙ ሲያስተምረን“ከእነዚህ ከታናናሾቹ አንዱን ስንኳ እንዳትንቁ ተጠንቀቁ፤ መላእክቶቻቸው በሰማያት ሁል ጊዜ በሰማይ ያለውን የአባቴን ፊት ያያሉ እላችኋለሁ” (ማቴ.18፡10) ብሎናል፡፡ እኛን ይጠብቁ ዘንድ የተሰጡን ቅዱሳን መላእክት ስለእኛ እንዲህ የሚቆረቆሩና ስለመዳናችን የሚተጉ ከሆነ በቅድስናው ልቆ የመላእክት አለቃ ሆኖ የተሾመው ቅዱስ ሚካኤል እንዴት ስለእኛ በእግዚአብሔር ፊት ይበልጥ አይቆም? (ሉቃ.13፡6-9) እንዴትስ በተሰጠው ሥልጣንና ኃይል አይረዳን? (መዝ.33፡7) እርሱ “ስለሕዝብህ ልጆች የሚቆመው”መባሉም እኛን በጸሎቱና በተራዳኢነቱ የጽድቅ ሕይወታችንን በሚገባ እንድናከናውን እንደሚራዳን የሚያሳይ ኃይለ ቃል ነው፡፡ የመልአኩ የቅዱስ ሚካኤል ጸሎቱና በረከቱ በእኛ ላይ ለዘለዓለሙ  ይደርብን አሜን፡፡

በዓለ ሲመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል በዓለ ሲመቱ ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ሚካኤል

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/790-2011-11-20-12-12-54