በዓለ ጥምቀት በጎንደር ከተማ

ጥር 12 ቀን 2007 ዓ.ም.

ዲ/ን ዘአማኑኤል አንተነህ /ከጎንደር ማእከል/

img 3695 ቤተ ክርስቲያን በዓለ ጥምቀትን የምታከብረው የበዓሉን ጥንታዊነት በጠበቀ መልኩ ሲሆን፤ ሀገራችን በዓለም እንድትታወቅና የበርካታ ጎብኝዎች መስሕብ እንድትሆን አድርጓታል፡፡ እንደመታደል ሆኖ ጎንደር ደግሞ የሊቃውንት መፍለቂያ ከመሆኗም በተጨማሪ ጥምቀት በድምቀት ይከበርባታል፡፡


የ2007 ዓ.ም. አከባበሩም የሚከተለውን ይመስል ነበር፡-


የከተራ በዓል
ጥር 10 ቀን 2007 ዓ.ም. እሁድ ጧት ቅዳሴ እንዳለቀ በመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ታቦታቱ በሰላም ወጥተው በሰላም እንዲገቡ የምሕላ የጸሎት ሥነ ሥርዓት ተከናውኗል፡፡ ይህ የምሕላ ሥነ ሥርዓት በየዓመቱ ይፈጸማል፡፡
5፡00 ላይ በሁሉም አድባራት 12 ጊዜ ደወል ተደውሏል፡፡


img 3574 6፡00 ሲሆን ወደ ጥምቀተ ባሕር የሚወርዱት ታቦታት የመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን፣ የደብረ ገነት አጣጣሚ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ የደብረ ጽባሕ እልፍኝ ቅዱስ ጊዩርጊስ ቤተ ክርስተያን፣ የደብረ ሰላም ፊት በር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን፣ የደብረ ኀሩያን አባጃሌ ተክለ ሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ታቦታት ከየመንበራቸው በመውጣት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ በሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ምእመናን ታጅበው መስቀል አደባባይ ላይ ተገናኝተዋል፡፡


የደብረ ስብሐት ቀሃ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ታቦት፣ በባሕረ ጥምቀቱ ውስጥ ባለው ቤተክርስቲያን የነበረውና አሁን በደብረ ስብሐት ቀሃ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን የሚገኘው የቅዱስ ፋሲለደስ ታቦት እና የመጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዮሃንስ ቤተ ክርስቲያን ታቦት ሆነው ዞብል አደባባይ አካባቢ ከፒያሳ የሚመጡትን እየተጠባበቁ ቆይተዋል፡፡


ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት ላይ ሁሉም ታቦታት ከተገናኙ በኋላ ወደ ጥምቀተ ባሕር ሲወርዱ ከታቦታቱ ፊት ዩኒፎርም የለበሱ የሰንበት ት/ቤት መዘምራን፤ ልብሰ ተክህኖ የለበሱ፤ ጽንሃሕ፤ መስቀል የያዙ ካህናትና ዲያቆናት፤ ግራና ቀኝ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የያዙ ወጣቶች፤ የጥምር መንፈሳዊ ወጣቶች፤ የወጣት እስካውት ሰልፈኞች፤ በባሕላዊ የሙዚቃ መሣሪያ /መሰንቆ/ የሚዘምሩ ባለሙያዎች፤ ከታቦታቱ ግራና ቀኝ የፖሊስ ሠራዊት አባላት እና የሥነ ሥርዓት አስከባሪዎች ተሰልፈው ተጉዘዋል፡፡


ከታቦታቱ በኋላም ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ የሰሜን ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እና የጎንደር ከተማ የመንግሥት አካላት፤ ካባ የለበሱ የደብር አስተዳዳሪዎችና አባት አርበኞች፤ ጥንግ ድርብ የለበሱ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና ካህናት፤ ምዕመናን እና ምዕመናት በእልልታ እና በዝማሬ እያጀቡ ዞብል አደባባይ ሲደርሱ ከፒያሳ ከመጡት ጋር ተገናኝተዋል፡፡


ታቦታቱ ወደ ባሕረ ጥምቀቱ እንደደሱም እለቱን የተመለከተ ያሬዳዊ ወረብ በእለቱ ተረኛ በደብረ ጽጌ መጥምቀ መለኮት ቅዱስ ዩሐንስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት፤ እንዲሁም የወንጌል ትምህርት በየተራ ቀርበዋል፡፡
በመጨረሻም ብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ ቃለ ምእዳን ሠጥተው ታቦታቱ ወደተዘጋጀላቸው የክብር ቦታ ገብተዋል፡፡


የማህሌቱና የቅዳሴው ሥነ- ሥርዓት
ከምሽቱ 2፡00 ሰዓት ጀምሮ በባሕረ ጥምቀቱ ውስጥ ከሚገኘው ቤተ ክርስቲያን በሊቃውንቱ ማሕሌት ሲደርስ አድሮ ከሌሊቱ 10፡00 የቅዳሴ ሥርዓቱ ቀጥሏል፡፡
የቅዳሴው ሥርዓት ከተጠናቀቀ በኃላም የወንጌል ትምህርት በሊቀ ሊቃውንት ዕዝራ ሐዲስ በመንበረ መንግሥት መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን የዐራቱ ጉባኤያት መምህር ተሰጥቶ በብፁዕ አቡነ ኤልሳ ፀሎት እና ቃለ ምዕዳን የመርሐ ግብሩ ፍፃሜ ሁኗል፡፡
ታቦታቱ ወደ ጥምቀተ ባሕሩ ሲወርዱ በታጀቡበት ሁኔታ ወደመጡበት አድባራትና ገዳማት ሲመለሱም በክብር በማምራት ወደ መንበረ ክብራቸው ገብተዋል፡፡


img 3534 የደብረ ገነት አጣጣሚ ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንና የደብረ ሰላም ፊት በር ቅዱስ ሚካኤል
ቤተ ክርስቲያን ሁለቱ ታቦታት እዚያው ባሕረ ጥምቀቱ ላይ አድረዋል፡፡


በበዓሉ በርካታ የውጭ ሀገር ጎብኝዎች የተገኙ ሲሆን፤ በርካቶቹ ነጠላና ባሕላዊ የኢትዮጵያውያን አለባበስ ለብሰው በዓሉን አድምቀውታል፡፡


በበዓሉ EBSን ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የተገኙ ሲሆን፤ የጎንደር ማእከል ሚዲያ ክፍልም በበኩሉ የቀረፃ ኮሚቴ አቋቁሞ ሙሉ መርሐ ግብሩን እየቀረጸ ሲሆን፤ የሚዲያ ክፍሉ በባሕረ ጥምቀቱ ለታደሙ ምአመናን በፕሮጀክተር የታገዘ አጠቃላይ የማኅበሩን ሥራዎች አሳይቷል፡፡


ቃና ዘገሊላ
በዚህ ዕለት ጠዋት የቅዳሴ ሥነ-ሥርዓት ከተከናወነ በኋላ 2ቱ የደብረ ገነት አጣጣሚ ቅዱስ
ሚካኤል ቤተ ክርስቲያንና የደብረ ሰላም ፊት በር ቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን ታቦታት
ለጉዞ ወደ መንበረ ክብራቸው ይወጣሉ፡፡ ከዚያም በቃና ዘገሊላ የሚለው ስብሐተ እግዚአብሔር ደርሶ
በየምዕራፉ በሊቃውንቱ ያሬዳዊ ወረብ እየቀረበ ታቦታቱ ወደ መንበረ ክብራቸው ይሄዳሉ፡፡ ታቦታቱ
መስቀል አደባባይ ሲደርሱ ትምህርተ ወንጌልና ቃልምዳን ይሰጣል፡፡ ከዚያም ደብረገነት አጣጣሚ ቅዱስ
ሚካኤል ወደ መንበረ ክብሩ ይገባና ደብረ ሰላም ፊት በርቅዱስ ሚካኤል ወደ መንበሩ ታጅቦ ይጓዛል፡፡
ከዚያም ከመንበረ ክብሩ ደርሶ ትምህርትና ቃለ ምዕዳን ተሰጥቶ የበሉ ፍፃሜ ይሆናል፡፡

 

በተያያዘ ዜና ጥር 18 ቀን እና ጥር 21 ቀን 2007 ዓ.ም ደግሞ በርዕሰ አድባራት አበራ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን እና በሎዛ ማርያም ቤተ ክርስቲያን ይኸው ደማቅ የጥምቀት በዓል ይደገማል፡፡

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1702-2015-01-20-10-28-05