የጥምቀት በዓል በድምቀት ተከበረ
- Details
- Created on Monday, 19 January 2015 02:50
- Written by ማሕበረ ቅዱሳን
ጥር 11 ቀን 2007 ዓ.ም.
በእንዳለ ደምስስ
የ2007 ዓ.ም. የጥምቀት በዓል ጥር 11 ቀን በመላው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በድምቀት ተከበረ፡፡
በተለይም በአዲስ አበባ ጃን ሜዳ ከከተራ በዓል በኋላ በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እለቱን የተመለከቱ ቀለማትና ምንባባት በዝማሬና በምስጋና እየቀረቡ፤ ማኅሌትና የቅዳሴ ሥርዓቱ በቅዱስ ፓትርያርኩና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት እየተመራ ተካሒዷል፡፡
ከለሊቱ 12፡30 ሰዓት ጀምሮ ቅዱስ ፓትርያርኩ፤ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ የመንግሥት ተወካዮች፤ አምባሳደሮች፤ ዲፕሎማቶች፤ የማኅበረ ቅዱሳንና የሰንበት ትምህርት ቤቶች መዘምራን፤ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ ሀገር ጎብኚዎችና ምእመናን በተገኙበት ጸሎተ ወንጌል በማድረስ፤ ጸበሉ ተባርኮ በቅዱስ ፓትርያርኩና ሊቃነ ጳጳሳት ለምእመናን የመርጨት ሥርዓት ተከናውኗል፡፡
የእለቱ ተረኛ የቀበና መካነ ሕይወት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንና የሰንበት ትምህርት ቤቱ መዘምራን እለቱን የተመለከተ ያሬዳዊ ወረብ፤ በፈረንሳይ ሌጋሲዮን ገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት የአጫበር ወረብ ቀርቧል፡፡
ቅዱስነታቸውም “ወደምሰሰ ለነ መጽሐፈ ዕዳነ፤ የዕዳችንን መጽሐፍ ደመሰሰልን” /ቆላ. 2፡14/ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል መነሻ በማድረግ እለቱን የተመከተ መልእክትና ቃለ ምእዳን ሰጥተዋል፡፡ ባስተላለፉት መልእክትም “የሰው ልጅና የሌሎች ፍጡራን መኖሪያ የሆነው ዓለም በኃጢአተ ሰብእ ምክንያት ክፉኛ ተበክሎ እስከ ልደተ ክርስቶስ 5500 ዓመታት ያህል በፍዳና በኩነኔ ተይዞ ቆይቷል፡፡
የእዳው መነሻ ኃጢአተ አዳም ቢሆንም ከእርሱ በኋላ የተነሱ ልጆቹም በተመሳሳይ ኃጢአተኞች ሆነው ስለቀጠሉ ችግሩ እየተባበሰና እየሰፋ መጥቶ ከነፍሳዊ ኩነኔ በተጨማሪ ምድርን በጥፋት ውኃና በእሳተ ገሞራና ሊያስቀጣ ችሏል፡፡ . .. . ከአዳም ጀምሮ እስከ ክርስቶስ ድረስ የነበረው ሰው ሁሉ ኃጢአተኛ ሆኖ ስለተገኘ በኃጢአት እዳው ከሚፈረድበት በቀር የሚድንበት መንገድ አልነበረምና የሰው ዘር ሁሉ ለኃጢአት ፍርድ የተጋለጠ ሆነ፡፡ ሮሜ.3፤23
እግዚአብሔር አምላክ እውነተኛ ፈራጅ፤ መሐሪና ይቅር ባይ ነውና በልጁ መስዋእትነት የሰው እዳ ኃጢአት ሰርዞ ሰውን በምሕረቱ የሚቀበልበት እድል እንዳመቻቸ በአፈ ነቢያቱ ገለጠ፡፡ ዘመኑም ሲደርስ ከቅድስት ድንግል ማርያም በሥጋ ሰብእ ተወለደ፤ ግእዘ ሕፃናትን ጠብቆ በየጥቂቱ አደገ፤ በ30 ዓመቱ በእደ ዮሐንስ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠመቀ፡፡ በዐራቱም ወንጌላውያን ትምህርትና ምስክርነት እንደተገለጠው ጌታችን ሲጠመቅ እግዚአብሔር አብ በብሩህ ደመና ላይ ሆኖ “ይህ የምደው ልጄ ነው፤ እርሱን ስሙት” ሲል መንፈስ ቅዱስ በነጭ እርግብ አምሳል ወርዶ ጌታችን ላይ ሲቀመጥ፤ ሰማያት ሲከፈቱ መታየታቸው እግዚአብሔር በአካል ሦስት መሆኑን፤ ኢየሱስ ክርስቶስም ከሦስቱ አካል አንዱ አካል መሆኑን ከመታወቁም በላይ ሰው ከእዳ ኃጢአት ነጻ ሆኖ በልጅነት ክብር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት የሚችልበት እድል ምን እንደሆነ በግልጽ ያመላከተበት ነው፡፡ ሰው በእምነትና በጥምቀት እግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት እንደሚችል ያረጋገጠበት ክስተት ነው” ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ከቅዱስ ሚካኤል ታቦታት በስተቀር ሌሎቹ ታቦታት በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፤ በሰንበት ትምህርት ቤት መዘምራንና ምእመናን እንደታጀቡ ወደየአብያተ ክርስቲያናቱ በክብር ተመልሰዋል፡፡
Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1701-2015-01-19-10-15-00