በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ደን ላይ የእሳት ቃጠሎ ደረሰ
- Details
- Created on Thursday, 15 January 2015 02:18
- Written by ቀዳሚ ገጽ
• እሳቱ የጠፋው ከቤተ ክርስቲያኑ በግምት በ50 ሜትር ርቀት ላይ ነው
ጥር 7 ቀን 2007 ዓ.ም.
በባሕር ዳር ማእከል
በጣና ኃይቅ በሚገኘው በዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም ደን ላይ ጥር 6 ቀን 2007 ዓ.ም ረፋድ ላይ የእሳት ቃጠሎ ደረሰ፡፡
በቦታው በመገኘትና የገዳሙን መነኮሳት በማነጋገር በተገኘው መረጃ መሠረት እሳቱ የተነሳው በግምት ከቀኑ 4፡30 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፤ የተነሳውን እሳት የገዳሙ መነኮሳት ማጥፋት ስላልቻሉ የገዳሙን ደወል በተደጋጋሚ ለመደወል ተገደዋል፡፡ የደወሉን ድምጽ በመስማት በቅርብ የሚገኙት ቁጥራቸው ሃምሳ የሚደርሱ የደቅ ደሴት ምእመናን በሁለት የሞተር ጀልባዎች ተሳፍረው ከመነኮሳቱ ጋር በመሆን ከፍተኛ እርብርብ አድርገዋል፡፡
እሳቱ የተነሳው ለማሳ ዝግጅት ምንጠራ እሳት በተጠቀሙ የገዳሙ መነኩሴ መሆኑንም የገዳሙ መነኮሳት ከመንግስት ተወካዮች ጋር ባደረጉት ውይይት ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለገዳሙ አገልግሎት ወደ ባሕር ዳር ከተማ በመጡ የገዳሙ መነኩሴ አማካይነት በጣና ኃይቅ የጀልባ አከራዮችና ባሕር ዳር ለሚገኙ ምእመናን መረጃው የደረሰው 5፡30 ሰዓት አካባቢ ሲሆን፤ ጉዳዩ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከባሕር ዳር ከተማ እስከ ክልልና ፌደራል የመንግሥት አካላት ድረስ ወዲያውኑ እንዲታወቅ ተደርጓል፡፡
ቃጠሎው በሁለት የቤተ ክርስቲያኑ አቅራቢያ ቦታዎች ላይ በሚገኘው ደን ውስጥ ባደረሰው ጉዳት በግምት 1 ሄክታር የሚሸፍኑ ቁጥቋጦዎችና ሸምበቆዎች የተቃጠሉ ሲሆን፤ እሳቱን መቆጣጠር የተቻለው በአቅራቢያው ለነበረው ሳር ጎጆ ቤት በግምት 15 ሜትር፤ ለቤተ ክርስቲያኑ ደግሞ በ50 ሜትር ቅርበት ላይ መሆኑን እሳቱን በማጥፋት ላይ ከነበሩ ምእመናን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
በእግዚአብሔር ቸርነት በገዳሙ ቤቶችና ቤተ ክርስቲያኑ ላይ ጉዳት ሳያደርስ እሳቱ ወደ 9፡00 ሰዓት አካባቢ በቁጥጥር ሥር ሊውል ችሏል፡፡
የመከላከያ ሠራዊት አባላት፣ የፖሊስና የመንግስት ተወካዮች፤ እንዲሁም ምእመናን ከቀኑ 7፡30 እስከ 8፡50 ሰዓት ባለው ጊዜ በ4 አነስተኛ እና 1 መካከለኛ የሞተር ጀልባዎች ተሳፍረው ከቀኑ 10፡20 እስከ 12፡00 ሰዓት ባለው ጊዜ በገዳሙ ደርሰዋል፡፡ በደረሱበት ሰዓትም እሳቱ ሙሉ በሙሉ በቁጥጥር ሥር ውሎ የነበረ ሲሆን፤ የመጣው ሰው የቀረውን በዐመድ ውስጥ የሚገኝ ረመጥ በማጥፋት ተሳትፏል፡፡
ገዳሙ ከባሕር ዳር ከተማ 44 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝና በጀልባ ከ2፡00 እስከ 3፡00 የሚወስድ በመሆኑ በቦታው በጊዜ ለመድረስና እሳቱን በማጥፋት ሥራ ላይ ለመሳተፍ አስቸጋሪ አድርጎታል፡፡ ወደ ገዳሙ ለመድረስ ርቀቱ ጊዜ ቢወስድም በደቅ ደሴት የሚገኙ ምእመናን ፣ የባሕር ዳር ከተማ ሀገረ ስብከት አባቶችና ምእመናን፤ የመንግሥት ኃላፊዎችና የመከላከያ ሠራዊት አካላት የነበራቸው ተግባራዊ ምላሽ ከፍተኛ ነበር፡፡ በተጨማሪም የክልሉ መንግስት ከፌደራል መንግሰት ጋር በመነጋገር እሳቱ በቁጥጥር ሥር ማዋሉንና የአካባቢው ኅብረተሰብ የተረጋጋ መሆኑን ለማረጋገጥ አንድ ሄሊኮፕተር በገዳሙ ዙሪያ ቅኝት አድርጎ ተመልሷል፡፡
የዳጋ እስጢፋኖስ ገዳም በ13ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በአቡነ ሂሩተ አምላክ የተመሠረተና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ከሚገኙ ጥንታዊ ፣ ታሪካዊና የብዙ ቅርሶች መገኛ ከሆኑት ገዳማት መካከል አንዱ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ ገዳም በርካታ ንዋያተ ቅድሳት፣ መጻሕፍት ፣ የነገሥታት ዘውዶች፤ አጽሞች እና ሉሎችም ቅርሶች መገኛ ነው፡፡
Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1693-2015-01-15-09-34-39