በአርባ ምንጭ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም የተገነባው የአብነት ትምህርት ቤት ርክክብ ተካሔደ

ጥር 5 ቀን 2007 ዓ.ም.

በደመላሽ ኃይለ ማርያም

arba በአርባ ምንጭ ደብረ ጽዮን ቅድስት ማርያም ገዳም የተገነባው የአብነት ትምህርት ቤት ብፁዕ አቡነ ኤልያስ  የጋሞ ጎፋ እና የደቡብ  ኦሞ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ  በተገኙበት ጥር 3 ቀን 2007 ዓ.ም ርክክብ ተካሔደ፡፡


በማኀበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኀበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል የተገነባው የአብነት ትምህርት ቤት ሠላሳ ሁለት (32) የአብነት ተማሪዎችን እና አራት (4) መምህራንን እንደሚያስተናግድ ብፁዕነታችው ጠቅሰው፤ የአብነት ትምህርት ቤቱን ቀሪ ሥራዎች በማጠናቀቅ የተማሪዎቹን ቁጥር ወደ መቶ ለማሳደግ ጥረት እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡


arba 01 የአብነት ትምህርት ቤቱ ዐራት የተለያዩ ሕንፃዎች ያሉት ሲሆን፤ ለተማሪዎቹ እና ለመምህራኑ የሚያገለግሉ ማደሪያ ክፍሎች፣ መማሪያ ክፍሎች፣ መመገቢያ ሰፊ አዳራሽ፣ ምግብ ማብሰያ፤ የገላ መታጠቢያ እንዲሁም መጸዳጃ ቤቶችን በማካተት በቂ ቁሳቁስ እንደተሟላላቸውና አነስተኛም ቢሆንም መተዳደሪያ በጀት እንዳለው የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኀሩያን ገሪማ ጌታነህ ገልጸዋል፡፡


የአብነት ትምህርት ቤቱን ለመገንባት የገንዘብ ወጪውን በማኀበረ ቅዱሳን ጠያቂነት እና አስፈጻሚነት ሙሉ ለሙሉ የሸፈነው በሰሜን አሜሪካ የሚገኘው የበዓለ ወልድ ማኀበር ሲሆን፤ የማኅበሩ ተወካይ ወ/ሮ ቤተልሔም “ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ይህንን የበረከት ሥራ ለመሥራት እድሉን ስላገኘንና ስለተሳካልን በማኅበሩ አባላት ስም አመሰግናለሁ፤ ወደፊትም አገልግሎታችንን አጠናክረን እንቀጥላለን” ብለዋል፡፡


በጋሞ ጎፋ እና ደቡብ ኦሞ አህጉረ ስብከት የሚሰጠውን መንፈሳዊ አገልግሎት ለማሳደግ እና ስብከተ ወንጌልን ለማስፋፋት ሰፊ አስተዋጽኦ ላለው ለዚህ አዳሪ የአብነት ትምህርት ቤት ግንባታ ከሁለት ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ መደረጉንም በማኀበረ ቅዱሳን የቅዱሳት መካናት ልማትና ማኅበራዊ አገልግሎት ዋና ክፍል ዳይሬክተር ዲያቆን አእምሮ ይሔይስ ተናግረዋል፡፡


በርክክብ መርሐ ግብሩ ላይ የአህጉረ ስብከቱን ሊቀ ጳጳስ ጨምሮ የሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኃሩያን ገሪማ ጌታነህ፣ የማኀበረ ቅዱሳን ተወካይ ሊቀ ትጉኀን ቀሲስ ዶክተር ሙሉጌታ ስዩም፣ የጋሞ ጎፋ ዋና አስተዳደሪ ተወካይ፤ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን እና በርካታ የአርባ ምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ተገኝተዋል፡፡

 

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1690-2015-01-13-13-40-30