የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር በቅድስት ጣራ ገዳም ተካሄደ

መጋቢት 2 ቀን 2007 ዓ.ም.

በግዛቸው መንግስቱ /ከባሕር ዳር ማእከል/

tara 11 በማኅበረ ቅዱሳን የሰሜን ምዕራብ ማእከላት ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የባሕር ዳር፣ ጎንደርና ደብረ ታቦር ማእከላትን በማስተባበር የካቲት 29 ቀን 2007 ዓ.ም በምእራፈ ቅዱሳን ቅድስት ጣራ አንድነት ገዳም የሐዊረ ሕይወት መርሐ ግብር አካሄደ፡፡


በዕለቱ በደን የተሸፈነው የቅድስት ጣራ አንድነት ገዳም ከሦስቱም ማእከላት፤ ከአካባቢው የሚገኙ የወረዳ ማእከላት አባላትን ጨምሮ በአጠቃላይ ከ3500 በላይ ምእመናን በክርስቲያናዊ አለባበስ ደምቀው፤ እንዲሁም ከ40 በላይ የሕዝብ ማመላለሻ አውቶቡሶችና በግል መኪናዎቻቸው በመጡ ተሳታፊዎች ተጨናንቋል፡፡ ምእመናን ገዳማቱን ከተሳለሙ በኋላ መርሐ ግብሩ በጸሎት ተጀምሯል፡፡


የማኅበረ ቅዱሳን የባሕር ዳር ማእከል መዘምራን የመርሐ ግብሩ መጀመሪያ የሆነውን ያሬዳዊ መዝሙር ካቀረቡ በኋላ በምእራብ ጎጃም ሀገረ ስብከት የዐራቱ ጉባኤያት መምህር ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ “ቤተ ሳይዳ” በሚል ርዕስ የምእመናን ሕይወት የሚዳስስ ሰፊ ትምህርት ሰጥተዋል፡፡ በምክረ አበው መርሐ ግብር በክፍል አንድ ለተጠየቁ ጥያቄዎችም በዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ሰፋ ያለ ምላሽና ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡


tara 22 ከስዓት በኋላ በነበረው መርሐ ግብር ትምህርተ ወንጌል በመምህር ብርሃኑ አድማስ “የማይበሉ” በሚል ርዕስ፤ በማኅበረ ቅዱሳን የደብረ ታቦር ማእከል መዘምራን የተክሌ አቋቋም፤ የቅድሰት ጣራ አንድነት ገዳም ታሪክና መልእክት በገዳሙ አበምኔት ቀርበዋል፡፡ የክፍል ሁለት የጥያቄዎች መልስም በሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክና ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡ መንፈሳዊ መነባንብ እና ያሬዳዊ ዝማሬ የመርሐ ግብሩ አካል ነበሩ፡፡


በመጨረሻም የደቡብ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ ሊቀ ኅሩያን ዮሐንስ መዝገቡ ለምእመናን መልእክታቸውን አስተላልፈው በጸሎት መርሐ ግብሩ ተፈጽሟል፡፡

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1771-2015-03-11-14-50-28