“ሰለ ቤተ ክርስቲያን ጸልዩ፤ ከእግራችን የሚተካ እንዲገኝ፤ እግዚአብሔር ተተኪ እንዳያሳጣን ጸልዩ”

/ብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ/

ነሐሴ 27 ቀን 2007 ዓ.ም

በእንዳለ ደምስስ

01abune kewst ነሐሴ 26 ቀን 2007 ዓ.ም የብፁዕ አቡነ ፊልጶስ የቀብር ሥነ ሥርዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከተፈጸመ በኋላ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ስብከተ ወንጌል አዳራሽ ወዳጅ ዘመዶቻቻውን ለማጽናናት መርሐ ግብር ተካሒዷል፡፡ በዚህ መርሐ ግብር ላይ ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ተገኝተው የነበረ ሲሆን፤ የማጽናኛ የወንጌል ትምህርት በብፁዕ አቡነ ቀውስጦስ የሰላሌ ፍቼ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተሰጥቷል፡፡


ብፁዕነታቸው በሰጡት የማጽናኛ ትምህርት፡-


ብፁዕ አቡነ ፊልጳስ የሔዱበትን ጎዳና ለመሔድ ሁላችንም በአፋፍ ላይ ነው ያለነው፡፡ ሥጋ ለባሽ የሆነ ሁሉ በዚህ ጎዳና ሳይሔድ የሚቀር የለም፡፡ ስንሔድ ግን ጎዳናችን ቀና እንዲሆን ክርስቲያናዊ ሕይወታችን የተስተካከለ መሆን አለበት፡፡ እርስ በርሳችን ፍቅር፤ ሰላም፤ አንድነት ሊኖረን ይገባል፡፡ ሰውን ከሚያስቀይም ሥራ፣ ክፉ ቃል ከአንደበታችን እንዳይወጣ ራሳችንን መቆጣጠር ያስፈልጋል፡፡ ሰው ሞቱን ካሰበ ክፉ አይሠራም፣ ሌላውን ለምን አሳዝናለሁ እያለ ክፉ ከመሥራት ራሱን ይጠብቃል፤ ለንስሓም የሚያበቃ ይህ ነው፡፡


ብፁዕነታቸው ራሳቸውን ይቆጣጠሩ እንደነበር እኛ ምሥክሮች ነን፡፡ ትልቅ አብነት የሆኑን አባታችንን ነው ያጣነው፣ ቢሆንም የድርሻቸውን ተወጥተው ሔደዋል፡፡


ብዙ አባቶቻችን ተለይተውናል እኛም ወደዚያው ነንና ከእግራችን የሚተካ እግዚአብሔር ይዘዝልን፡፡ ስለ ቤተ ክርስቲያን ጸልዩ፤ ከእግራችን የሚተካ እንዲገኝ እግዚአብሔር ተተኪ እንዳያሳጣን ጸልዩ በማለት ተናግረዋል፡፡

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/1978-2015-09-02-08-43-39