የምሥጢር ቀን

ነሐሴ 12 ቀን 2007 ዓ.ም.

ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መላክ

በምዕ/ጐጃም ሀገረ ስብከት የ፬ቱ ጉባኤያት መምህር

የምሥጢር ቀን የአምላክ ሰው መሆን አንዱ ምክንያት ምሥጢረ መለኮት ለተሰወረበት ዓለም ምሥጢረ መለኮትን መግለጥ ነው፡፡ ክፉውንና ደጉን ለይቶ ከሚያስታውቀው ዛፍ የተነሳ ከ8ኛ መዐርግ ላይ ሆኖ በመፈጠሩ የተሰጠውን ከፍተኛ የዕውቀት ጸጋ ክፉ ዕውቀት ስለተጨመረበት ለነፍሱ ምሥጢረ መለኮትን ማወቅ የሰው ልጅ ተስኖት ነበር ፡፡ ጌታችን ወደዚህ ዓለም ሲመጣ ዓለም ምንም ምሥጢር የላትም ነበር፡፡ ምሥጢራት ሁሉ በልበ መለኮት ተሰውረው ይኖሩ ነበር እንጂ፡፡ በሌላ አነጋገር የተፀነሰ ምሥጢር እንጂ የተወለደ ምሥጢር አልነበረም ማለት ነው፡፡ ለዚህ አይደል መድኀኒታችን እየሱስ ክርስቶስ ለደቀ መዛሙርቱ ከሕዝብ ለይቶ ምሥጢራትን ይነግራቸዉ የነበረው ማቴ.13 ፥11፡፡ በቀዳማዊው ሰው በአዳም በኩል ለሰው ልጀች ሁሉ የተሰጠው የመንግሥቱ ምሥጢር ዳግም በሁለተኛው ሰው በክርስቶስ በኩል ካልተገለጠ በሌላ በምን ይገለጣል!! ለዚህም በአብ ልብነት ተሰውሮ ይኖር የነበረው ብቸኛ ምሥጢር እርሱ ሆኖ ሳለ ከልደቱ ጀምሮ የመንግሥቱን ምሥጢር በብዙ መንገድ ገለጠ፡፡


ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደተናገረው ለቀደሙት ሰዎች በብዙ መንገድ በብዙ ኅበረ አምሳል ምሥጢራትን ይናገር የነበረ እግዚአብሔር አወጣጡ ከጥንት በሆነውና ተቀዳሚ ተከታይ በሌለው በአንድ ልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ተናገረን ዕብ 1፥1-2 ፡፡ ማንም ያየው የሌለ እግዚአብሔርነቱን ወደ ዓለም መጥቶ ተረከው፡፡ በልደቱ ቀን ከገለፀልን የተነሣ “ስብሐት ለእግዚአብሔር በሰማያት” ብለን ዘመርን፡ እግዚአብሔር ገለጠልን፡፡ “ይህንን ምሥጢር እናይ ዘንድ ኑ! እስከ ቤተልሔም እንሒድ” ሉቃ.2፡15 ብለው ሲናገሩ ከእረኞች አፍ መስማታችንስ ልደቱ ሊያዩት የሚገባ ምሥጢር መሆኑን የሚያሳይ አይደል፡፡ የሶርያው ሊቅ ቅዱስ ኤፍሬም ይህን ሲያፀናልን “ንዑ ርዕዩ ዘንተ መንክረ ይህን ድንቅ ምሥጢር ታዩ ዘንድ ኑ!” በማለት ምሥጢርነቱን በማወጅ ሕዝቡን ይጠራል፡፡


በሰው ሊገለጥ ያለው ምሥጢር ይህ ብቻ አልነበረም፡፡ በቤተ ኢያኢሮስ በአደረገው የማዳን ሥራ ምሥጢረ ድኅነትን፤ በቤተ አልዓዛር በአደረገው ሞትን የማሸነፍ ሥራ ምሥጢረ-ትንሣኤ ሙታንን፤ ወዙ እንደ ደም ወይቦ እስኪወርድ ድረስ በጌቴ ሴማኒ ምሥጢረ ጸሎትን ካሳየ በኋላ ደገኛውን ምስሥጢር በዕለተ አርብ መጋረጃው ተቀዶ የሰው ልጅ ባሕረ እሳትን ተራምዶ እስክናይ ድረስ ታላቅ ምሥጢርን በደብረ ታቦር ገለጠልን፡፡


ጌታ ሊገልጠው የፈለገውን ማንኛውንም ምሥጢር ሦስት ነገሮችን መምረጥ የሁልጊዜ ተግባሩ ነው፡፡ ምሥጢሩን የሚገልጥበት ቦታ፣ ጊዜ እና ሰው ናቸው፡፡ በደብረ ዘይት የገለጠውን በደብረ ታቦር፣ በጌቴ ሴማኒ የገለጠውን በዮርዳኖስ፤ ለነቢያት የገለጠውን ለሐዋርያት አይገልጠውም፡፡ በተለይ በሐዋርያት ልቦና ቆልፎ ያኖረውን ከሁሉም በላይ ደግሞ በእመቤታችን ልቦና የሰወረውን ምሥጢሩን ማን ያውቀዋል?? አበው እንደነገሩን በልበ ሐዋርያት ተሰውሮ የቀረውን የወንጌል ምሥጢር እስከ ዓለም ፍፃሚ የሚያውቀው የለም ብለውናል፡፡ ምክንያቱም የሐዋርያትን ክብር ከላገኙ ሐዋርያት ያወቁትን ማወቅ ስለማይቻል ነው፡፡ ከሐዋርያት በኋላ ተነስቶ ወደ ሐዋርያት መዐርግ መድረስ ከተቻለው ከቅዱስ ጳዉሎስ በቀር የተሳካለት ማንም የለም፡፡ ዛሬ ክብር ይግባውና መድኃኒዓለም ክርስቶሰ በደቀ መዛሙርቱ ልብ ሊያስቀምጠው የፈለገው አንድ ታላቅ ምሥጢር አለው በጊዜው ጊዜ የሚነገር ከትንሣኤ በኃላ በሚዘከር እንጂ በማንኛውም ጊዜ የማይነገር አዲስ ምሥጢር ነው፡፡ ታዲያ ለዚህ ታላቅ ምሥጢር መገለጫ ትሆን ዘንድ የተመረጠችው ደግሞ ደብረ ታቦር ተራራ ናት ፡፡


ደብረ ታቦር ለምን ተመረጠ?

1.ትንቢቱ፤ ምሳሌው ሊፈፀም፡-

በቀደመው ዘመን ነቢያት ትንቢት ከተናገሩላቸዉ ቅዱሳት መካናት አንዱ ደብረ ታቦር ነው፡፡ ነቢዩ ዳዊት በመዝሙሩ “ታቦር ወአርሞንኤም በስመ ዚአከ ይትፌስሑ ታቦርና አርሞንኤም በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል” መዝ፡ 188÷12 በማለት ከደብረ ታቦር እስከ አርሞንኤም በደረሰው የመለኮት ብርሃን የተፈጠረውን ደስታ ሲገልጥ እንሰማዋለን፡፡ ምንድን ነው ይህ ደስታ? ሊባል ይችላል፡፡ ነብዩ ከአንድ ሺህ ዓመት በኋላ ስለሚደረገው ተራሮችንና ኮረብቶችን ሳይቀር ያስፈነደቀ ደስታ በእውነት ይህን ተናገረ፡፡ ምናልባት “በአንተ ስም ደስ ይላቸዋል” ብሎ ለሰው በሚናገር መልኩ ግዑዛን ለሆኑ ተራሮች መናገሩ ሊያስገርም ይችል ይሆናል፡፡ የሰው የደስታው መገለጫ የገፁ ብሩህነትም አይደል? እነዚህም ተራሮች በዚህ ዕለት በተገለጠው የመለኮታዊ ክብሩ ነፀብራቅ ጨለማ ተወግዶላቸዉ የፀሐይን ብርሃን በሚበዘብዘው አምላካዊ ብርሃን፣ ብርሃን ሆነው የዋሉበት ቀን ነውና ነቢዩ ለሰው በሚናገርበት ግስ ይናገርላቸዋል፡፡ ሌላም ምሥጢር አለው ይላሉ ሊቃውንቱ፡፡

በተራሮች ስም የተጠሩት ልዑላኑ የጌታ ደቀ መዛሙርት ነቢያትና ሐዋርያት እና ልዑላኑ አገልጋዩችህ በጌታ ስም ደስ ይላቸዋል ማለት ነው ብለውታል፡፡ ምሳሌ በአባቶቻችን ዘመን በዚህ ቅዱስ ተራራ ጽኑ ሰልፍ እንደተደረገ የመሳፍንቱ ታሪክ በተፃፍበት መጽሐፍ እናነባለን መሳ.4 ፥1፡፡ በእሥራኤል ላይ ገዥ ሆኖ የተነሣው በክፉ አገዛዙም ምክንያት እሥራኤልን ያስለቀሰው አሕዛባዊው የሠራዊት አለቃ ድል የተነሳው በዚሁ ሥፍራ ነበር፡፡ ደብረ ታቦር 9 የብረት ሠረገሎች የነበሩትን ባለ ሠራዊት ሰው ሲሳራን ድል ለማድረግ ምቹ ቦታ ነበር፡፡ ያውም በጥቂት ኃይል በሴቲቱ ነብይት በዲቦራ በሚመራ የጦር ሰራዊት ፡፡ ይህ በእውነት በኋለኛው ዘመን ለሚደረገው የድል ዘመን ጥላ አባቶቻችንን በብረት በትር ቀጥቅጦ የገዛውን ባለ ብዙ ሠራዊት ዲያብሎስን ከሴቲቱ ነብይት የተወለደው የይሁዳ አንበሳ ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ ቅዱስ ሥፍራ ድል እንደሚያደርግላቸዉ እሥራኤል ዘነፍስም ነፃ እንደሚያወጣቸው የሚያሳይ ምሥጢር ነበረው፡፡ ሲሳራን፤ ባራቅ እና ዲቦራ ድል ያደርጉታል ተብሎ ታስቦ ነበርን ? ይልቁንም ሲገዛን ሊኖር አስቦ አልነበረምን? የድንግል ልጅ መድኀኒታችን ክርስቶስ ግን የሲዖልን በሮች ሰብሮ ጠላታችንን በጽኑዕ ሥልጣን አስሮ እኛን ነፃ አወጣ፡፡ ታዲያ ምሳሌው አማናዊ የሚሆንበትን ዘመን መድረሱን ሊያበስራቸዉ ወደ ደብረ ታቦር ወጣ፡፡


2.ደብረ ታቦር ሁሉን የሚያሳይ ቦታ ስለነበር፡-

ደብረ ታቦር ሆኖ ዓለምን ቁልቁል መመልከት ይቻላል፡፡ የተራራው ጫፍ ላይ ሆኖ ሲመለከቱ ሁሉም ግልጥ ነው፡፡ ለዚህ ነው ቅዱስ ዼጥሮስ በዚህ ቦታ መኖርን የተመኘው “ሠናይ ውዕቱ ለነ ሀልዎ ዝየ- በዚህ መኖር ለእኛ መልካም ነው” (ማቴ.17÷4) ሲል ነበር ፍላጐቱን የገለጠው፡፡ ከሁሉ በላይ ሆኖ ሁሉን እያዩ ሚኖሩበት ከፍ ያለ ቦታ ነውና፡፡ እግዚአብሔር ግን ይህንን በምሥጢር አደረገ፡፡ ከዘመናት አስቀድሞ የተሰወረውን ምሥጢር ለሁሉ ግልጽ ሊያደርግ አስቦ ሁሉን ወደሚያሳየው ቦታ ወሰዳቸዉ፡፡ በክርስቶስ ሰው መሆን ያልታየ ምሥጢር ያልተገለፀ ድብቅ ነገር የለምና፡፡ ለዚህ አፈ- በረከት ተብሎ የሚጠራው ቅዱስ ኤፍሬም በረቡዕ ውዳሴ ማርያም ላይ “የማይታወቅ ተገለጠ የማይታይ ታየ” ሲል የተናገረው፡፡ አሁን የማይታየውን እግዚአብሔርን የምናይባት ድብቁን የእግዚአብሔርን ነገር በእምነት የምናስተውልባት አማናዊቷ የታቦር ተራራ ቤተ ክርስቲያን፡፡ በእርሷ ውስጥ የሚኖሩ ሁሉ ዓለምን ቁልቁል እየተመለከቱ ጣዕሟን ሲንቁባት ይኖራሉ፡፡ ከሷ ተለይቶ ከላይ ሆነው ከተራራው ጫፍ ስለሚመለከቷት ቤታቸዉን በተራራው ለማድረግ ይመኛሉ፡፡ ሁልጊዜም “እግዚአብሔርን አንዲት ልመና ለመንሁት እሷንም እሻለሁ በሕይወቴ ዘመን ሁሉ በእግዚአብሔር ቤት እኖር ዘንድ” መዝ ፡ 26፡4 እያሉ ይዘምራሉ፡፡ ምክንያቱም በዚህ ዓለም ውስጥ ሁኖ ታቦርን ማየት አይቻልም፡፡ በታቦር ላይ ሆኖ የዓለምን ምሥጢር ማወቅ ይቻላል፡፡


3.በተራራ የተነጠቅነውን ጸጋ በተራራ ለመመለስ

አዳም እንደ አጥቢያ ኮከብ የሚያበራ ግርማው የሚያስፈራ ብርሃናዊ ፍጡር እንደ ነበር፤ ስነ ተፈጥሮውን የሚናገሩ መጻሕፍት ምስክሮቻችን ናቸዉ፡፡ ይህንን ብርሃናዊ የጸጋ ልብሱን ተጐናጥፎ የተቀመጠው በእግዚአብሔር ተራራ በገነት ነበር፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮ የጠላት ዐይን አርፎበት ኖሮ ከጥቂት ዓመታት በኋላ ይህን ብርሃናዊ ልብሱን ለብሶ እንደ ማለዳ ኮከብ ሲያበራ መኖር አልተቻለውም፡፡ እናም በዚያው በእግዚአብሔር ቅዱስ ተራራ ላይ ሳለ ይህን ጸጋውን ባለማወቅ ተገፈፈ፡፡ የክርስቶስ ወደዚህ ዓለም መምጣት የተቀማነውን ለማስመለስ አይደል፡፡ ስለዚህም በዚህ ቅዱስ ተራራ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ በገለጠው ብርሃን ላይ ተስፋን አስጨበጠን፡፡ ቅዱስ ወንጌል እንደተናገረው በዚህ ዕለት ሐዋርያት ነቢያት በተገኙበት በዚህ ሥፍራ የክርስቶስ ሦስት ክንድ ከስንዝር አካሉ ብሩህ ሆነ፤ ልብሱም ከበረዶ ይልቅ ነጭ ሆነ፡፡

የሰው ልጅ ከቅዱስ ተራራ ከገነት ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ እንዲህ ሆኖ አያውቅም፡፡ ሰውነቱ በኀጢአት በልዞ በበደል መግነዝ ተገንዞ የሚያስቀይም መልክ ነበር እንጂ እንደዚህ የአማልእክት ልጆችን አይነት መልክ መች ነበረው? ዛሬ ግን እንደዚያ አይደለም፡፡ የአዳም አካል መልኩ ተለውጧል፡፡ ከጥቁረቱ ነጥቷል፡፡ ወንጌላውያን ይህን ሲገልጡት “ወተወለጠ አርአያሁ በቅድሜሆሙ፣ መልኩ በፊታቸዉ ተለወጠ” ማቴ17፥2፤ማር 9፥2፡፡ ኢትዮጵያዊ ቄርሎስ ተብሎ የሚጠራው የሀገራችን ሊቅ ቅዱስ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ ይሄን ሲተረጉም ክርስቶስ በዚህ ዕለት የተገለጠው አዳም ከበደል በፊት በነበረው መልኩ እንደነበረ መጽሐፈ ምስጢር በተሰኘው ድርሳኑ ይናገራል፡፡ ያማ ባይሆን ኖሮ ደብረ ታቦር እንደምን ልፍረስ አልፍረስ አላለችም፡፡ ምክንያቱም ሊጦን በተሰኘው ምስጋናችን ውስጥ ስለእግዚአብሔር ስንናገር የምንለውን እናውቃለን፡ “ዘይገሥሶሙ ለአድባር ወይጠይሱ - ተራሮችን በእጁ ሲዳስሳቸው የሚጤሱት” ብለን አይደል የምናመሰግነው፡፡


ታቦር ታዲያ እንደምን አልተናወጠችም? ለሙሴ እንኳን በተገለጠበት በዚያ በመጀመሪያው ተራራ የተደረገው እንደዚህ አልነበረም፡፡ ሕዝቡ የሚደርሱበትን አጥተንው እስኪንቀጠቀጡ ድረስ ከባድ የመብረቅና የነጐድጓድ ድምፅ በተራራው ላይ ነበር ዘጸ.19÷18፡፡ የዛሬው ግን ከዚያ ልዩ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከተገለጠው ክብር የተነሳ በዙሪያ የነበሩትን እንደ በድን ያደረገ የብርሃን ነፀብራቅ ቢኖርም ቅሉ ለቀደመው ሰው ለአዳም ከመርገም በፊት የነበረውን የጸጋ ግርማ ሞገስ የሚያሳይ ነው እንጂ ሌላ ምን ይሆናል? አብርሃም ዮርዳኖስን ተሻግሮ የተገናኘውን ሰው የመልከጸዴቅን ግርማ በአይኖቹ መመልከት አልችል ብሎ መልከጸዴቅ ቀርቦ እስኪያነሳው ድረስ በፊቱ እንደ በድን ሆኖ የወደቀ አይደለምን? ከእግዚአብሔር ይነጋገር የነበረው የሙሴን ፊት ማየት ተስኗቸዉ የእስራኤል ልጆች አልፈሩምን? ይህማ ምን ይገርማል በእውነቱ ይህ ሁሉ የሆነው በቅዱሱ የእግዚአብሔር ተራራ በገነት የተነፈግነው ልጀነታችንን የሚያስፈራና የሚያስደነግጥ ግርማ ሞገሳችንን እንደመለሰልን ለማጠየቅ ነው፡፡ በመጀመሪያው ሰው ያጣነው የልጅነት መልካችንን በሁለተኛው ሰው አገኘነው፡፡


ዛሬ እስከ ዓለም ፍፃሜ ድረስ በቤተ ክርስቲያን በኩል ይህ ዕድል ሲታደል ይኖራል፡፡ ወንዶቹ በ4ዐ ቀን ሴቶቹ በ8ዐ ቀን ወደ ቤተ ክርስቲያን መጥተው በማየገቦ ተጠምቀው ዳግመኛ ከብርሃን ተወልደው ሰይጣንን የሚያስደነግጥ መልክ ይዘው እንደሚመለሱ በፍትሕ መንፈሳዊ በ3ኛው አንቀጽ ተመዝግቧል፡፡


ያስተውሉ!! ደብረ ታቦር የቤተ ክርስቲያን ምሳሌ ናት፡፡ በደብረ ታቦር ነቢያትና ሐዋርያት መዐስባንና ደናግል፣ አረጋውያንና ወጣቶች እንደተገኙ ሁሉ ቤተ-ክርስቲያንም በነቢያትና በሐዋርያት መሠረት ላይ የታነፀች ናት፡፡ ለመዐስባንና ለደናግል፣ ለአረጋውያንና ለወጣቶች የተዘጋጀች የእግዚአብሔር መገለጫ ተራራ ነቸ፡፡ ከነቢያት 2ቱ ከሐዋሪያት 3ቱ መገኘታቸዉ ዛሬ በቤተ መቅደስ የሚያገለግሉት አምስት ልዑካን ምሳሌ ነው፡፡ እነዚያ ክርስቶስን እንደ ታቦት በመሀል አድርገው ነበር የተገኙት፡፡ በቤተክርስቲያንም በቃል ኪዳኑ ታቦት ዙሪያ የክብሩን ዙፋን ከበው የሚቆሙት አገልጋዮች በነዚያኞቹ አምሳል የቆሙ ናቸው፡፡

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-24/--mainmenu-26/1961-2015-08-18-13-43-48