በዲላ ማረሚያ ቤት አዳዲስ አማንያን የሥላሴ ልጅነትን አገኙ

የካቲት 3 ቀን 2008 ዓ.ም

ከዲላ ወረዳ ማእከል

01dilla የዲላ ወረዳ ማእከል ትምህርትና ሐዋርያዊ አገልግሎት ክፍል ከሰንበት ትምህርት ቤቶች ጋር በመተባበር በዲላ ማረሚያ ቤት ያስተማሯቸውን 48 ኢ አማንያን የነበሩ የሕግ ታራሚዎች ተጠምቀው የሥላሴ ልጅነትን አገኙ፡፡


የዲላ፣ ወናጎና ቡሌ ወረዳዎች ሥራ አስኪያጅ መልአከ ምሕረት ቆሞስ አባ ተክለ ዮሐንስ በላቸው የሕግ ታራሚዎቹ በዲላ ማረሚያ ተቋም ውስጥ በማኅበረ ቅዱሳንና በሰንበት ትምህርት ቤቶች እገዛ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርት ተምረው ለዚህ ታላቅ ክብር በመብቃታቸው ሁላችንም ልንደሰት ይገባል ብለዋል፡፡


01dilla hawa የሕግ ታራሚዎች ባሉበት ሆነው ንስሐ መግባት እንዲችሉ፣ እንዲማሩና ኪዳን እንዲያደርሱ በሀገረ ስብከቱ መልካም ፈቃድ አንድ ካህን መቀጠራቸውን የጠቆሙት ሥራ አስኪያጁ ወደፊትም ባሉበት ሆነው ሥጋ ወደሙን መቀበልና መጠመቅ እንዲችሉ፣ በማረሚያ ቤት ቤተ ክርስቲያን ለማሠራት ዝግጅቱ እየተጠናቀቀ እንደሆነና ለዚህም ከፍተኛ እገዛ ያረገላቸውን የዲላ ማረሚያ ቤት አስተዳደርን አመስግነዋል፡፡


የማስተማርና የማጥመቅ አገልግሎቱን በተመለከተም ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና ከማሰጠት በተጨማሪ አዳዲስ አማንያን በእምነታቸው ጸንተው እንዲኖሩ የማድረጉ አገልግሎት አነስተኛ በመሆኑ የክትትሉ ጉዳይ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል በማለት አሳስበዋል፡፡


የወረዳ ቤተ ክህነቱ ዋና ጸሐፊ ዲ/ን አልዓዛር ለማ ባስተላለፉት መልእክት ትምህርት በማስተማርና የቅርብ ክትትል በማድረግ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረገውን ማኅበረ ቅዱሳን የዲላ ወረዳ ማእከልን አመስግነው፤ የዲላ ከተማና የአካባቢው ሰንበት ትምህርት ቤት አባላትና ምእመናን የሕግ ታራሚዎችን በመጠየቅና በማጽናናት ይህን መልካም ፍሬ ማየት በመቻሉ ደስታው የሁሉም መሆኑን ተናግረዋል፡፡


አያይዘውም ከአሁን በፊት የተጠመቁትንና አዲስ ተጠማቂያንን እንዲበረቱ ትክክለኛውን መንገድ በመምረጥ ተጠምቃችኋልና የያዛችሁትን እምነት አጽንታችሁ ልትጠብቁና ለሌሎች የሕግ ታራሚዎችም ምሣሌ በመሆን ልትኖሩ ይገባል በማለትም አባታዊ ምክራቸውን ለግሰዋል፡፡ በበዓሉ ላይ ለተገኙት ምእመናንም የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ወገኖቻችን ወደዚህች ሃይማኖት ሊመጡ ችለዋል፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በደስታ ልንቀበላቸው፣ ልንከባከባቸውና ልንደግፋቸው ይገባል€ ሲሉ አሳስበዋል፡፡


ከተጠማቂዎቹ መካከል የሆነው ትግሉ ብሩ ወደ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት እንዴት ሊመጣ እንደቻለ ለቀረበለት ጥቄ ሲመልስ €œከልጅነቴ ጀምሮ ያደግሁት በሌላ ሃይማኖት ውስጥ ነበር፡፡ ነገር ግን በእግዚአብሔር ቸርነት ማረሚያ ቤት ከገባሁ በኋላ መንፈሳዊ የሆኑ ጓደኞችን በማግኘቴ የቅድስት ቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ሃይማኖት እንድማር ተነሳሳሁ፡፡ የዘላለም ሕይወት የማገኘው በኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት እንደሆነና ቀዳማዊት እምነት መሆንዋን በመረዳት ለመጠመቅ ችያለሁ፡፡ ወደፊትም በተማርኩት ትምህርት ያላመኑትን በማስተማርና በተሰጠኝ ጸጋ እግዚአብሔርን አገለግላለሁ ብሏል::

በማኅበረ ቅዱሳን ሐዋሳ ማእከል የዲላ ወረዳ ማእከል ሰብሳቢ የሆኑት አቶ አራርሳ ቦኪ በበኩላቸው ባስተላለፉት መልእክት በማረሚያ ተቋሙ የተደረገው የማስተማርና የማጥመቅ አገልግሎት 3ኛ ዙር መሆኑን ጠቁመው፤ ከዚህ በፊት በመጀመሪያው ዙር 27፣ በ2ኛው ዙር 24፣ እንዲሁም አሁን ደግሞ 48 በአጠቃላይ 97 የሕግ ታራሚዎች ከተለያዩ እምነቶች ወደ ጥንታዊት፣ ዘላለማዊት፣ ኵላዊት፣ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት መምጣታቸውን አስታውሰዋል፡፡ በእምነታቸው እንዲጸኑም ወረዳ ቤተ ክህነቱ፣ ሰንበት ትምህርት ቤቶች፣ የዲላና አካባቢው ምእመናንም እገዛቸው እንዳይለያቸው አሳስበዋል፡፡


ከተጠማቂዎቹ መካከል 46ቱ በዲላ ጌዴኦ ዞን ዲላ ማረሚያ ተቋም ውስጥ የሚገኙ የሕግ ታራሚዎች ሲሆኑ ሁለቱ የአካባቢው ነዋሪዎች ናቸው፡፡


የሕግ ታራሚዎቹ በሚጠመቁበት ዕለት ካህናት አባቶች፣ መምህራነ ወንጌል፣ የማኅበረ ቅዱሳን አባላት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችና ሌሎችም ምእመናን ተገኝተዋል፡፡

 

Read more http://www.eotcmk.org/site/-mainmenu-18/2072-2016-02-11-11-21-21