- Written by አቶ አብርሃም ሰሎሞን
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የርእሰ አድባራት ጽርሐ አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል መስከረም ፯/፳፻፱ ዓ.ም. ቁጥራቸው ከሁለት መቶ ሃምሳ ለሚበልጡ ሕፃናት በተጠናከረ መልኩ የአማርኛ ቋንቋ እና የአብነት ትምህርት መስጠት ጀመረ። ይኽ መደበኛ ትምህርትም በወጣለት የትምህርት መርሐ ግብር መሠረት ዘወትር ቅዳሜ ከጠዋቱ አራት ሰዓት እስከ ስድስት ሰዓት ድረስ (10:00 A.M. - 12:00 P.M.) ለሁለት ሰዓታት ይሰጣል። በዓመት ሁለት ጊዜ ከመስከረም ፯/፳፻፱ ዓ.ም. እስከ ታኅሣሥ ፳፪/፳፻፱ ዓ.ም. (Sep. 17, 2016-Dec. 31, 2008) እንዲሁም ከሦስት ሳምንታት ዕረፍት በኋላ ከጥር ፲፫/፳፻፱ ዓ.ም. እስከ ግንቦት ፲፪/፳፻፱ ዓ.ም. (Jan. 21, 2017-May, 20, 2017) የሚሰጠውን ትምህርት ለማስተማር ልምድና ፍላጎት ያላቸው የቤተ ክርስቲያኒቱ አባላት ከስብከተ ወንጌል ክፍሉ ጋር በመሆን ትምህርቱን ለመስጠት ተዘጋጅተዋል።
ነህምያ የፈረሰችውን ኢየሩሳሌምን ከሠራ በኋላ አሁን ደግሞ ሕዝቡ መሠራት አለበት በማለት መላውን ሕዝብ ሃይማኖታቸውን፣ ሥርዓታቸውን፣ እምነታቸውንና ማንነታቸውን ጠንቅቀው እንዲያውቁ ከነቢዩ ከዕዝራ ጋር ሆኖ መሠረት በመጣል በእምነትና በሃይማኖት ታሪካቸውን እንዲጠብቁ አድርጓቸዋል። እኛም እግዚአብሔርን የምናመልክበትንና ሃይማኖታችንን የምንማርበትን ቤተ ክርስቲያን ሠርተን ተተኪ ሕፃናትና ወጣቶች የሚማሩበትን መንገድ ካላመቻቸን የነህምያ ልጆች ስለማንሰኝ መላው ምእመናን የነገ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ የሆኑ ልጆቻቸውን በእምነት፣ በሃይማኖትና በምግባር ማሳደግ እንዲችሉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን እንዲህ ያለውን ማዕድ አዘጋጅታለች።
የዚህ ትምህርት ዓላማም ተማሪዎች የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖታቸውን፣ ትውፊታቸውንና ሥርዓተ አምልኳቸውን፣ ቤተ ክርስቲያን የምትጠቀምባቸውን ሃይማኖታዊ ትምህርቶች ውዳሴ ማርያም፣ መልክአ ማርያም፣ መልክአ ኢየሱስ፣ ግብረ ዲቁና፣ ተሰጥኦና መዝሙረ ዳዊትን እንዲሁም የአገራቸውን ባሕልና ታሪክ ጠብቀው በሥነ ምግባር ታንጸው በመኖር የአማርኛ ቋንቋን በሚገባ ማንበብና መጻፍ ችለው የማንነታቸው መገለጫ የሆነውን ሃይማኖታቸውንና የአገራቸውን ታሪክ አውቀውና ተረክበው ለተተኪው ትውልድ እንዲያስተላልፉ ማስቻል ነው።
ይኽ በ፳፻፰ ዓ.ም. የተጀመረው የአማርኛ ቋንቋና ሃይማኖታዊ ትምህርት እጅግ ውጤታማ የሆነና ብዙዎች ልጆቻቸው የእራሳቸውን ቋንቋ ሳይናገሩና ሃይማኖታቸው የሚገለጽበትን መጻሕፍትን ሳያነቡ መቅረታቸው ያሳዘናቸው ወላጆች ራሳቸውን ቀና እንዲያደርጉ ከማስቻሉም በላይ የልጆቹ ፍላጎት መጨመርና ለሃይማኖታቸው ቀናዒ መሆን ደግሞ የበለጠ ፍሬያማ እንዲሆን አስችሎታል።
በቤተ ክርስቲያን አባቶችና በስብከተ ወንጌል ክፍሉ እንዲሁም በሰንበት ት/ቤቱ የሕፃናት ክፍል ፍላጎትና ተነሣሽነት የተጀመረው ትምህርት በዚህ በያዝነው በ፳፻፱ ዓ.ም. የበለጠ መልክ ይዞ ቀጣይነት እንዲኖረው ለማስቻል የሕፃናት ክፍሉ ቅዳሜ መስከረም ፳፩/፳፻፱ ዓ.ም. ለሁለት ሰዓታት ጊዜ በመውሰድ የተሳካ ትምህርት ለተማሪዎች ለመስጠት ከተማሪዎች፣ ከአስተማሪዎችና ከወላጆች ምን ይጠበቃል በሚል ርእስ የውይይት መድረክ ፈጥሮ በርካታ ወላጆች ተሳትፈውበታል።
ባለ ሃያ አምስት ነጥቦች መመሪያ ይዞ ወላጆችን ያሳተፈው ይኽ ጉባኤ ወላጆች ያላቸውን አመለካከት የተረዳበትና ወደፊትም አሁን ከሚደረገው በላይ ታላቅ ሥራ መሠራት እንደሚገባው ያመላከተ ሆኖ ተገኝቷል። ከሁለት መቶ ሃምሳ በላይ የሆኑ ተማሪዎችን ለማስተናገድ ፍላጎቱና ዝንባሌው በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በወላጆች መካከል ቢኖርም ሁሉንም ተማሪዎች በሚፈልገው ዓይነት ፍጥነት ለማስተማር ግን የቦታው ጥበት የማያፈናፍን ሆኖ ተገኝቷል። በአንድ ክፍል ውስጥ እጅግ በርካታ ቁጥር ያላቸው ተማሪዎችን (ሕፃናት) ለማስተማር አዳጋች በመሆኑ ወላጆች ወደፊት ቤተ ክርኢስቲያኒቱ ተጨማሪ ክፍሎችን እስከምታሟላ ድረስ የወላጆች ተሳትፎ አስፈላጊነቱ ስለታመነበት በእያንዳንዱ ክፍል የበጎ ፈቃድ አገልጋዮች ከወላጆች መካከል ተመርጠው ማገልገል እንዳለባቸው ታምኖበታል።
ተማሪዎችን ለማስተማር በር ከፍተን የተለያዩ ልምምድ ማድረጊያ የሚሆን የቤት ሥራና የክፍል ሥራ ለመስጠት አንዳንድ አስፈላጊ የትምህርት መስጫ ቁሳቁስ መሟላት ስለሚገባቸውና ተማሪዎቹም ቢያንስ ዳቦና ውኃ በየሳምንቱ ለቁርሳቸው እንደሚያስፈልጋቸው በማመን እያንዳንዱ ወላጅ በየሴሚስተሩ ሃያ ዶላር ለመክፈል ተስማምቷል። የሚሰበሰበው ገንዘብም ወረቀት፣ የማባዣ ቀለም፣ ክላሰር/ፎልደር፣ ማርከር፣ እርሳስ፣ ላጲስ፣ እስኪሪብቶ፣ ፖስታ፣ ደብተር እና ሌሎች የትምህርት መሣርያዎች እንዲሁም ዳቦ እና ውኃ ለመግዣ ይውላል። እንዲህ ያለው ከወላጆች ጋር መሰባሰብና ውይይት ማድረግ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደተሻለ ደረጃ እንደሚያደርሰን እምነት አለን።
ይኽ በደብራችን የሚሰጠው ትምህርት ቤተ ክርስቲያን ለልጆቿ ልታደርግላቸው ከሚገባት ጉዳይ አንደኛውና ዋነኛው ነው። ተማሪዎቹ ለየክፍለ ጊዜው የተዘጋጀውን ሥርዓተ ትምህርት በተገቢው መንገድ እንዲከታተሉና በፈተናው እንዲያልፉ ወላጆች ማስጠናትና የቤት ሥራቸውን አብሮ በመሥራት ማሳየት እንደሚጠበቅባቸው በመተማመንና ለተማሪዎቹ እድገት የወላጆች አስተዋጽዖ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ የጋራ ሥራ ሠርተን የነገ ተረካቢ የሆኑ ሕፃናትን ማፍራት እንድንችል ባደረግነው ውይይት ታላቅ መሠረት እንደጣልንበት እናምናለን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
አብርሃም ሰሎሞን