በሰንበት እና በዘወትር ቅዳሴ አገልግሎት ከምዕመናንም ዘንድ ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ (COVID-19 Church Re-opening Guidelines)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!
COVID-19 በመባል የሚታወቀው ተላላፊና ቀሳፊ በሽታን ለማስወገድ ብቸኛው አማራጭ ጥንቃቄ መውሰድና የጋራ ኃላፊነትን በጋራ መወጣት መቻል ነው። ከሚመለከተው ክፍል መመሪያ መቀበልና የተሰጠውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረግ ያለንን አገልግሎት ስኬታማና ውጤታማ ያደርግልናል። በመሆኑም ጊዜው ከፈጠረው ችግር በመነሣት ሁላችን የአገልግሎቱ ተካፋይ እንድንሆን በማሰብ ሰበካ ጉባኤው ከዚህ በታች በዝርዝር የተጻፉትን መመሪያዎች አውጥቷል፤ ለተግባራዊነቱም የእናንተን ትብብር አጥብቆ ይሻል፦
በሰንበት እና በዘወትር ቅዳሴ አገልግሎት ላይ የሚሰጥ አገልግሎትን በተመለከተና ከምዕመናንም ዘንድ ሊደረግ ስለሚገባው ጥንቃቄ፦
፩) የሚያስላችሁ ከሆነ፣ የትንፋሽ ዕጥረት ወይም የመተንፈስ ችግር ከገጠማችሁ፣ ትኩሳት ካለባችሁ፣ ብርድ ብርድ ካላችሁ፣ በተደጋጋሚ የሚያንቀጠቅጥ ብርድ ከያዛችሁ፣ የጡንቻ ሕመም፣ ራስ ምታት፣ የጉሮሮ መቁሰል፣ የማጣጣም ወይም የማሽተት ስሜት ካጣችሁና በኮቪድ 19 በሽታ ለተያዘ ታማሚ ከተጋለጣችሁ ለእናንተም ሆነ ለሌሎች ጤንነት ስትሉ ከቤት እንድትቆዩ እንጠይቃለን።
፪) ምናልባት ከምትሠሩበት መሥሪያ ቤት፣ ከምትውሉበት ቦታ፣ ከምትኖሩበት መኖሪያ አካባቢና ውስጣችሁ ከሚሰማችሁ ሁኔታ አንፃር የእናንተ መምጣት ስጋት ሊሆን ይችላል ብላችሁ ካሰባችሁ መምጣት የለባችሁም።
፫) ለቅዳሴ አገልግሎት ወደ ቤተ ክርስቲያን መግባት የሚችሉት ተረኞች የሆኑና በሰበካ ጉባኤው አማካኝነት የስም ዝርዝራቸው ተጽፎ እንዲመጡ የታዘዙት ብቻ ናቸው።
፬) በአዘቦት ቀን ቅዳሴ የመጣችሁና ያስቀደሳችሁ ሰዎች ያለውን ጫና ለመቀነስና ሌሎችም ተጠቃሚ እንዲሆኑ በእሑድ ዕለት ቅዳሴ ላይ ባለመምጣት ልትተባበሩን ይገባል።