ለተገደለው Mr. GEORGE FLOYD የተሰማን ጥልቅ ኀዘን
ይኽ ከፍተኛ ቁጣ የቀሰቀሰው ዜና ከተሰማበት ቀን ጀምሮ በማንኛውም የዓለም ዜና መሰራጫ እየተላለፈ ከትንሽ እስከ ትልቅ ድረስ ሁሉም አይቶት፤ ከአዳጊ ወጣቶች ጀምሮ እስከ አረጋውያን ድረስ ሁሉም በድርጊቱ አዝኖ ደረቱን በቁጭት ሲደቃና ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ውስጥ ገብቶ በኃይል መነሣቱን ተመልክተናል።
ዛሬ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን፦
* ይኽንን እኲይ ግብር ፍጹም ኀዘን በተሞላው ሁኔታ ትገልጸዋለች።
* የምታስተምረው ወንጌል እንዲህ ያለውን ድርጊት ያወግዛልና በፍጹም ትኮንነዋለች።
* ኃይልዋም ጉልበትዋም እግዚአብሔር ነውና ሁሉን ማድረግ ወደሚችለው አቤት ትላለች።
* ልጆቿን ሰብስባ ታጽናናለች፤ ትመክራለች፤ ታስተምራለች።
* ለተገፋውና ለወደቀው ድምጽ ናትና በሞት ለተለየው ጸሎትዋን ወደ አምላክዋ ታቀርባለች።
* ፍጹም መጽናናት የሚገኘው ከእግዚአብሔር ነውና ፍትህ በምድር ላይ ነግሦ እንዲኖር ያለማቋረጥ ወንጌለ ክርስቶስን ትሰብካለች።
* የምታስተምራቸው ልጆቿ ወደፊት የሰላም አምባሳደር ሆነው በዓለም ስማቸው እንዲጠራና በመልካም ሥነ-ምግባር ታንጸው ምሳሌ እንዲሆኑላት ትፈልጋለች።
* ልጆቿ የችግር ሳይሆን የመፍትሔ አካል ሆነው ዘረኝነትን በመዋጋት «ሰው ተብሎ የተጠራ ሁሉም የእግዚአብሔር ፍጥረት ያለ አድልዎ በእኩልነት እንዲኖር ከሚያስቡና ከሚሠሩ ሰዎች መካከል እንደ አንዱ ሆነው እንዲታዩላት ታበረታታለች።
* ወጣቶች ኀዘናቸው ሲያበቃ ወደፊት ምን ማድረግ አለብን በማለት በታላቅ ራእይ ተነሥተው ከበጎ ነገር ጋር የሚተባበሩና ራስን በመግዛት አትራፊ እንዲሆኑ ጥሪዋን ታቀርባለች።
ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከላይ ከብዙ በጥቂቱ የተዘረዘሩትን ነጥቦች ለልጆችዋ ስትገልጽ ልጆችዋ በዚህ ፋና ብርሃን ዕንቅፋቱን እያለፉ መውደቃቸውን ሳይሆን መነሣታቸውን፣ ማዘናቸውን ሳይሆን ደስታቸውን፣ ጅማሬአቸውን ሳይሆን ፍጻሜያቸውን አስበው እንዲጓዙላት በማሰብ ነው።
በመጨረሻም ቤተ ክርስቲያን ይኽንን እኲይ ተግባር የምታወግዘው የሕይወት መመሪያ ይሆንልን ዘንድ በተሰጠን መጽሐፍ ቅዱስ ላይ እግዚአብሔር ከሚጠላቸው ድርጊቶች አንዱ ንጹሕ ደም ማፍሰስ በመሆኑ ነው። አምስቱ ውሾች ተብለው ከተጠቀሱት መካከል አንዱ ነፍሰ ገዳይነት ስለሆነ ነው። ከአሥራ ስድስቱ የሥጋ ሥራዎች አንዱ መግደል ሆኖ ስለተጠቀሰ ነው። ከአሥርቱ ትዕዛዛት አንዱ አትግደል ስለሚልም ነው።
አሁንም ይኽንን እኩይ ምግባር እየተዋጋን ከመለያየት ይልቅ ወደ አንድነት የምንመጣበት መንገድ ላይ እየሠራን መኖርን መለማመድ ያስፈልገናል። መለያየቱ የሚጎዳን ሁላችንንም ስለሆነ በተቻለ መጠን ከላይ እንደገልጽነው የመፍትሔው አካል በመሆን ከችግሩ የምንማርበት እንጂ ተስፋ የምንቆርጥበት እንዳይሆን እናሳስባለን። ወላጆች ወደ አሜሪካን ምድር በተለያዩ ዓይነት ሁኔታዎች ከተለያዩ ቦታዎች መጥተን ነዋሪ ብንሆንም ልጆቻችን ደግሞ በዚህ ምድር ተወልደው የትውልድ አገራቸው ሆኗልና አስተማማኝ ፍትህ ነግሦ ሰው በጥፋቱ እንጂ በቀለሙ ምክንያት የማይቀጣበት፣ የማይጉላላበትና የማይገደልበት ምድር እንዲኖረን ሁላችን በጋራ ልንመክርበት ያስፈልገናል።
በተለይ ልጆቻችንን በሚማማሩበት እና በሚሠሩበት ቦታ ያለ ምንም መሳቀቅ መኖር የሚችሉት ችግሩን ብቻ ሳይሆን መፍትሔውን ፈላጊዎች ሆነው መትጋት ሲችሉ ብቻ ነውና በመምከርና በማስተማር ወላጆች የድርሻችንን እንወጣ፤ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ዘወትር በጸሎትዋ እያገዘች ለዘላለም ትኑር።
ለሟች ቤተሰብ ልዑል እግዚአብሔር መጽናናት እንዲሰጥልን ያለውም የሰላም መደፍረስ ተወግዶ ሰላማዊ የሆነ ኑሮ እንድንጀምር አምላካችን ይርዳን።
ወስብሐት ለእግዚአብሔር!!!