- Written by ዶ/ር ሰሎሞን ፎሌ
ጸሎት፤ የሰው ልጅ እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት፣ ምህረት እና ቸርነቱን የሚለምንበት፣ የሚማለድበት እና የሚማፀንበት እንዲሁም እግዚአብሔር የሰውን ልመና ተቀብሎ ፈቃዱን የሚፈጽምበት ረቂቅ ምስጢር ነው። የጸሎት መሠረቱ “ዕሹ ታገኛላችሁ ለምኑ ይሰጣችኋል ደጁን ምቱ ይከፈትላችኋል” (ማቴ. ፯፡፯) የሚለው የጌታችን ትምህርት ነው።
በቤተ ክርስቲያናችን ከሚጸለዩ ጸሎቶች የሚዘወተረው አጭር ጸሎት “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ፤ አቤቱ ክርስቶስ ሆይ ማረን” የሚለው ሲሆን ካህኑ ሲናዝዙ አሥራ ሁለት ጊዜ “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” ካዘዙ በኋላ “በእንተ ማርያም መሐረነ ክርስቶስ፤ አቤቱ ክርስቶስ ሆይ ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ብለህ ማረን” በሉ ይሉናል፡፡ አባቶች እንደሚያስተምሩን ይህ ጸሎት ፍጹም ኃይል ያለዉና ከጽድቅ ጎዳና ሊያወጡን የሚራወጡ አጋንንትን የምንመክትበት ጋሻችን ነዉ። ስንጸልይም በዘልማድ የሚሆን ማነብነብ ሳይሆን ሕዋሳትን በመሰብሰብ በሰቂለ ሕሊና በነቂሐ ልቡና መሆን አለበት፡፡ ልባችን ከአፋችን: አፋችን ከልባችን አንድ ሳይሆን፥ ከመንፈስ የተራቆተ ስሜት የማይሰጥ ትርጉም የለሽ ዝብዘባ እንዳይሆን ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ይገባናል፡፡
የእግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ ጸሎት በቤተ ክርስቲያን የሚዘወተርበት እና በተለይ ገዳማውያን አባቶችና እናቶች በስፋት የሚጠቀሙበት አራት ዋና ምክንያቶች አሉ፦
፩. ሁሉም ሰዉ ሊያስታዉሰዉ የሚችል ቀላል ጸሎት መሆኑ፣
፪. የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም በመጥራት መንፈሳዊ ኃይል እና ፍጹም ደስታ የምናገኝበት መሆኑ፣
፫. ሐሳባችንን በመሰብሰብ ደጋግመን ልንጸልየዉ ስለምንችል ወደ እግዚአብሔር ያቀርበናል። ፩ኛ ተሰ ፭፡፲፯- ፲፰ እንደሚለዉ “ሳታቋርጡ ጸልዩ፤ በሁሉ አመስግኑ፤ ይህ የእግዚአብሔር ፈቃድ በክርስቶስ ኢየሱስ ወደ እናንተ ነውና”።
፬. ሙሉ ጸሎት መሆኑ።
እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” እንደምን ሙሉ ጸሎት ሆነ ቢሉ ወንጌልን በአጭሩ የያዘ በመሆኑ ነው፡፡ በጣም አጭር በሆነ ዐረፍተ ነገር ሁለቱን አእማደ ምሥጢራት ይዟል፤ ምሥጢረ ሥጋዌ እና ምሥጢረ ሥላሴን! በመጀመሪያ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን እግዚእ በማለት ጌታችን እና ገዥ አምላክ መሆኑን ፤ ክርስቶስ ስንልም መሲሕ፡ ሥጋን የተዋሐደ መንግሥቱ የማያልፍ እውነተኛ ንጉሥ እና አምላክ ብሎ መመስከር ይህ ነገረ ክርስቶስ ነው፡፡
በሌላ መልኩ የጌታ ወዳጅ ወንጌላዊው ዮሐንስ “ወልድን የሚክድ ሁሉ አብ እንኳ የለውም፤ በወልድ የሚታመን አብ ደግሞ አለው” እንዳለ (፩ኛ ዮሐ. ፪፥፳፫) ፤ ቅዱስ ጳውሎስም “በመንፈስ ቅዱስም ካልሆነ በቀር ኢየሱስ ጌታ ነው ሊል አንድ እንኳ እንዳይችል አስታውቃችኋለሁ” እንዳለ የአብም የመንፈስ ቅዱስም ነገር አለበት (፩ኛ ቆሮ. ፲፪፥፫)። “መሐረነ” ስንልም የእግዚአብሔርን ክብር ከመመስከር ጋራ ንስሐ፣ ኀዘን፣ ራስን ማዋረድ፣ ኀጢአተኝነትን ማመናችንን የሚያመለክት ነው፡፡ በመሆኑም “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” እያልን ስንጸልይ በደለኝነታችንን አምነን በተሰበረ ልብ መሆን አለበት። ይህን ተረድቶ የሚጸለይ ጸሎት እግዚአብሔር የሚቀበለው እውነተኛ ጸሎት ይሆናል፤ ኀጢአትን መደምሰስ የሚችል ይቅር ባይ አምላክም ምህረት ያደርግልናል። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ እንዳመለከተን፡- “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፥ የተሰበረውንና የተዋረደውን ልብ እግዚአብሔር አይንቅም” (መዝ. ፶(፩) ፥፲፯)።
ጌታችንም በወንጌል ትክክለኛ የጸሎት ስልት ምን እንደ ሆነ በፈሪሳዊና በቀራጭ ምሳሌ አስተምሯል። “ጻድቃን እንደ ሆኑ በራሳቸው ለሚታመኑና ሌሎቹን ሁሉ በጣም ለሚንቁ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፥ ሁለት ሰዎች ሊጸልዩ ወደ መቅደስ ወጡ፥ አንዱ ፈሪሳዊ ሁለተኛውም ቀራጭ። ፈሪሳዊም ቆሞ በልቡ ይህን ሲጸልይ፡- እግዚአብሔር ሆይ፥ እንደ ሌላ ሰው ሁሉ፥ ቀማኞችና ዓመፀኞች አመንዝሮችም፥ ወይም እንደዚህ ቀራጭ ስላልሆንሁ አመሰግንሃለሁ፤ በየሳምንቱ ሁለት ጊዜ እጦማለሁ፥ ከማገኘውም ሁሉ አሥራት አወጣለሁ አለ። ቀራጩ ግን በሩቅ ቆሞ ዓይኖቹን ወደ ሰማይ ሊያነሣ እንኳ አልወደደም። ነገር ግን አምላክ ሆይ፥ እኔን ኃጢአተኛውን ማረኝ እያለ ደረቱን ይደቃ ነበር። እላችኋለሁ፥ ከዚያ ይልቅ ይህ ጻድቅ ሆኖ ወደ ቤቱ ተመለሰ፤ ራሱን ከፍ የሚያደርግ ሁሉ ይዋረዳልና፥ ራሱን ግን የሚያዋርድ ከፍ ይላል” (ሉቃ. ፲፰፥፱-፲፬)። “እግዚኦ መሐረነ ክርስቶስ” የሚለው ጸሎትም በቀራጩ የልብ ትሕትና ምሳሌነት የተዘጋጀ ፍፁም ንስሐዊ ጸሎት ነው።
በቤተ ክርስቲያናችን የብዙዎች ጸሎት ከእግዚአብሔር ምላሽ እንዳገኘ በየሣምንቱ እሁድ በአዉደ ምህረት ይነገረናል። ዘወትር ከቅዳሴ በኃላ የዕለቱን መርሐ ግብር ስንጀምር ከሚተላለፉ መለዕክቶች ዋነኛው እገሌ የሚባሉ ምዕመን “ጸሎቴ ደረሰ፣ልመናዬ ተሰማ እግዚአብሔርን አመስግኑልኝ" ብለዋል ካሉ በኋላ ካህኑ በቤተ ክርስቲያን የተገኘውን ሕዝብ እንዲህ ሲሉ ይጠይቃሉ፦
"እርሳቸዉን የሰማ አምላክ የእናንተንም ጸሎት ይስማ፤ ሴቶች በዕልልታ ወንዶች በጭብጨባ እግዚአብሔርን አመስግኑላቸዉ” ይላሉ። ዘወትር ይህንን መልዕክት ስንሰማ ልናስተዉል የሚገባን ብዙ ምዕመናን ጸሎታቸዉን በሰቂለ ኅሊና በአንቃዕድዎ ማለትም ዐይንን ወደ እግዚአብሔር በማንሳት እና ሳያቋርጡ ዘወትር በትጋት እንደሆነ ነዉ። ከእነዚህ ሰዎች የምስክርነት ቃል የምንረዳዉ ጸሎታችን ከንቱ ጩኸት አለመኾኑን እና ጊዜያችንም በከንቱ አለመጥፈቱን ነዉ።
ቤተ ክርስቲያናችን እንደምታስተምረው ጸሎታችን ተሰሚ ልመናችንም ተፈጻሚ የሚሆነው ሰውነታችንን ከበደል ልቡናችንን ከቂም ከበቀል እንዲሁም ከተንኮል ንጹሕ አድርገን ስንጸልይ ነው። ለዚህም የተጣላነውን ታርቀን፣ የበደልነውን ክሰን፣ የቀማነውን መልሰን መገኘት እንዳለብን ዘወትር ይነገረናል።
ቅዱስ ዮሐንስ በወንጌሉ (ዮሐንስ ፲፭፡፯) “በእኔ ብትኖሩ ቃሎቼም በእናንተ ቢኖሩ የምትወዱትን ሁሉ ለምኑ ይሆንላችሁማል” ይላል። ከዚህ የምንማረዉ ጌታን መታዘዝ ለጸሎታችን መመለስ ወሳኝ መሆኑን ነው። ከዚያም 1ኛ ዮሐንስ ፫፡፳፪ እንደሚለው ትዕዛዙን የምንጠብቅና በፊቱ ደስ የሚያሰኘውን ስናደርግ የምንለምነውን ሁሉ ከእርሱ እንደምናገኝ በግልጽ ያስረዳናል። በአጠቃላይ ለእግዚአብሔር ቃል ብንታዘዝ እግዚአብሔር ጸሎታችንን ይሰማል። ዓመጸኞች ከሆንን ግን ጸሎታችን አይሰማም። አለመታዘዝ በደል ነው፤ በደል ደግሞ ጸሎት እንዳይመለስ እንቅፋት ይሆናል።
የስሙ ቀዳሽ የክብሩ ወራሽ ለመሆን በኃጢአት ያደፈውን ሰውነታችንን በንስሐ አጥበን በንጽሕና እና በቅድስና በፊቱ ቆመን የምንጸልይ ያድርገን! አሜን!
በዶ/ር ሰሎሞን ፎሌ