- Written by ሊቀ ብርሃናት ቀሲስ ሄኖክ ያሬድ
ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደ በሠላሳ ዓመቱ ለድኅነተ ዓለም አንድም ለአብነት በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቋል። ያጠመቀውም ዮሐንስ ወልደ ዘካርያስ ነው። በተጠመቀ ጊዜ የባሕርይ አባቱ አብ በደመና ሆኖ "በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው" ብሎ መስክሮለታል። መንፈስ ቅዱስም በጸዓዳ ርግብ አምሳል በራሱ ላይ ተቀምጧል። ማቴ፣ ፫፥ ፲፫–፲፯
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ቅዱስ ዕለት በዓል ሠርታ በየዓመቱ በማኅሌትና በቅዳሴ በተለየ ሁኔታ ታከብረዋለች። ይህ በዓል በሚከበርበት ጊዜ በዋዜማው ታቦታቱ ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወጥተው በወንዝ ዳር /በሰው ሰራሽ የውሃ ግድብም ቢሆን/ በዳስ በድንኳን ያድራሉ። ሌሊት ስብሐተ እግዚአብሔር ሲደርስ አድሮ ሥርዓተ ቅዳሴውም ይፈጸማል። ሲነጋ በወንዙ ዳር ጸሎተ አኰቴት ተደርሶ አራቱም ወንጌላት ከተነበቡ በኋላ ውኃው ተባርኮ ለተሰበሰበው ሕዝብ ይረጫል። አንዳንድ ደካሞች የጠበሉን መረጨት አይተው "የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ታጠምቃለች" ብለው የሚተቹ አሉ። ነገር ግን የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በየዓመቱ ይህን የምትፈጽመው ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለእኛ ብሎ ያሳየውን ትሕትና ለመመስከርና፣ ምዕመናንን የጌታን በረከተ ጥምቀት ለማሳተፍ እንጂ የተጠመቁትን ምዕመናን እየመላለሰች በየዓመቱ አታጠምቅም።