አዲሱ ዓመት

አዲሱ ዓመት - ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንዳስተማረው (ክፍል ፩)

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ ነሐሴ ፳፬ ቀን፣ ፳፻፮ ዓ.ም.)፡- በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!!!

የምወዳችኁ ልጆቼ! አዲሱ ዓመት የደስታ የሰላምና የጤና እንዲኾንላችኁ ትሻላችሁን? እንኪያስ ገና ከዥመሩ በስካር፣ በዘፈን፣ በገቢረ ኀጢአት ለማሳለፍ አታቅዱ፡፡ የአዲሱ ዓመት የመዠመሪያውን ዕለት ብቻ ሳይኾን እያንዳንዱን ቀን በገቢረ ኀጢአት አትዠምሩት፡፡ እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ ሥራ፣ ምግባር ትሩፋት በመሥራት አሐዱ በሉ እንጂ፡፡ ዕለታት ክፉዎች ወይም ጥሩዎች የሚኾኑት በተፈጥሮአቸው እንደዚያ ኾነው አይደለም፡፡ ዕለቱን ክፉ ወይም ደግ እንዲኾን የምናደርገው እኛው ነን፡፡ የአምናው ማግሰኞ ከዘንድሮ ማግሰኞ የተለየ አይደለም፡፡ የተለየ የሚያደርገው የእኛ ብርታት ወይም ስንፍና ብቻ ነው፡፡

የጽድቅን ሥራ የምንሠራበት ከኾነ አዲሱ ቀን ብቻ ሳይኾን አዲሱ ዓመት ለእኛ መልካም ነው፡፡ ኀጢአት የምንሠራበት ከኾነ ግን ቀኑ ብቻ ሳይኾን አዲሱ ዓመትም ክፉና መከራ የመላበት ይኾንብናል፡፡ አዲሱን ዓመት በበጐ ሥራ የምንዠምረው ከኾነ በዓመቱ በምናደርገው ማንኛውም ክንውን ላይ በጐ ተጽዕኖ ያሳድርብናል፡፡ በትግሃ ሌሊት፣ በቀዊም፣ በጾም በጸሎት እንድንበረታ ስንቅ ይኾነናል፡፡ በስካር፣ በዘፈን፣ በኀዘን የምንዠምረው ከኾነ ግን ዓመቱ ሙሉ እንዲኽ የተጐሳቈለ ዓመትን እናሳልፋለን፡፡ ሕይወታችንን በከንቱ እንገፋለን፡፡ ዲያብሎስም ይኽን ጥንቅቅ አድረጐ ስለሚያውቅ ዓመቱን በገቢረ ኀጢአት እንድንዠምረው እየቀሰቀሰ ነው፡፡ ፈቃዳችንን አጥፍቶ፣ ዓይነ ልቡናችንን አሳውሮ በዘፈን፣ በስካር፣ በዋይታ እንድንዠምረው በተለያየ መንገድ እየለፈፈ ነው፡፡

Please click here to open the pdf.

ሰነፍ ሰው “ቀኑ ክፉ ወይም መልካም የሚኾነው ነው፡፡በእኔ ምክንያት አይደለም” ብሎ ያምናል፡፡ እንዲኽ በማመኑም ክፉ ነው ብሎ በሚያስበው ቀን ገቢረ ጽድቅ መሥራት እንደሚቻል አያስብም፡፡ ቢያደርግም ትርጕም እንደሌለው አድርጐ ይቈጥሯል፡፡ የጽድቅ ሥራ ለመሥራት በተመቻቸለት ቀንም ልል ዘሊል ከመኾኑ የተነሣ ምግባር ትሩፋት ለመሥራት አይሽቀዳደምም፡፡ ስንፍናው ምን ዓይነት ጉዳት እንደሚያመጣበት አይረዳም፡፡ ድኅነቱን ሳይፈጽም ዕድሜውን ኹሉ በከንቱ ይገፋል፡፡ እንዲኽ ያለ የሥጋም የነፍስም ጕዳት እንደሚያገኘው ዲያብሎስ ዓይነ ልቡናውን ስለሚያሳውርበት ከአጋንንት ወጥመድ ለመሸሽ ዓቅምን ያጣል፡፡

ዲያብሎስም ዕለት ዕለት ይኽን እንዳንገነዘብ በተለያየ ማጥመጃ መንገዶች እኛን ለመጣል ይሯሯጣል፡፡ አንዱ መንገድም ስለ ክርስትና ሕይወታችን ግድ እንዳይኖረን ማድረግ ነው፡፡ በዚኽም ክርስቲያናዊ ተፈጥሮአችንን ያሳጣናል፡፡ የእግዚአብሔርን ሥራ በገቢር እንድንሰድብ ያደርገናል፡፡ ነፍሳችንን በቆሸሸ ስፍራ ተወሽቃ እንድትቀር ያደርጋታል፡፡ የምወዳችኁ ልጆቼ! እኛ ግን ይኽን ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ በዓለም ላይ ከኀጢአት በቀር ክፉ ነገር እንደሌለ ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ ከምግባር ከትሩፋት በቀርም መልካም ነገር እንደሌለ ልናውቅ ልንረዳ ይገባናል፡፡ በዚኽም ዘወትር እግዚአብሔርን ደስ አሰኝተን ልንኖር እንዲገባን ማወቅ መረዳት ይገባናል፡፡ መጠጥ ደስታን አያመጣም፤ ደስታን የሚያመጣው ጸሎት ነው፡፡ ደስታን የምናገነኘው ቃለ እግዚአብሔርን ከመስማት እንጂ ከስካር አይደለም፡፡ ስካር የነፍስ መታወክን ያመጣል፤ ቃሉን መስማት ግን ተመስጦን ያመጣል፡፡ ስካር ሁካታን ያመጣል፤ ቃሉን መስማት ግን ሁካታን ያርቃል፡፡ ስካር ዓይነ ልቡና እንዲጨልም ያደርጋል፤ ቃለ እግዚአብሔር ግን የጨለመው ዓይነ ልቡናችን ብሩህ እንዲኾን ያደርጋል፡፡ ስካር የኀጢአት ጓዝ ይዞ ይመጣል፤ ቃለ እግዚአብሔር ግን አዲስ የሚመጡትን ብቻ ሳይኾን የነበሩትንም ያስወግዳል፡፡

ልጆቼ! የዚኽን ዓለም ደስታ ንቆ ሰማያዊ ደስታን እንደመሻት ያለ ጥበብ ምንም የለም ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ይኽን ገንዘብ የምናደርግ ከኾነ፣ ለሰማያዊ ሕይታችን ቅድሚያን የምንሰጥ ከኾነ የዚኽ ዓለም ዝባዝንኬ ቢቀርም አይከፋንም፡፡ አንድ ሰው ባለጸጋ ስለኾነ ቅናት አይይዘንም፡፡ ምንም ምድራዊ ሀብት ባይኖረንም ድኾች እንደኾንን አናስብም፡፡ ባለ ጸጋውን ክርስቶስ የያዘ ሰውስ እንዴት ድኻ ይባላል? በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ በዓል ማድረግ ማለትም ይኸው ነው፡፡ እግዚአብሔር የሚወዳችኁ አንድም እግዚአብሔርን የምትወዱት ሆይ! አንድ ክርስቲያን በዓልን ሲያከብር ሳምንትን ወይም ወርን ወይም ዓመትን ጠብቆ መኾን የለበትም፡፡ ከክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ጋር እንደሚስማማ አድርጐ ዕለት ዕለት በዓል ሊያደርግ ይገቧል እንጂ፡፡ ከክርስቲያናዊ ተፈጥሮው ጋር የሚስማማ በዓል ማለትስ ምን ማለት ነው? ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ምን እንደሚለን አብረን እናድምጠው፡- “በቅንነትና በእውነት ቂጣ በዓልን እናድርግ እንጂ በአሮጌ እርሾ በክፋትና በግፍ እርሾም አይደለም” /1ኛ ቆሮ.5፡8/፡፡ ንጽሐ ልቡናን ገንዘብ ያደረገ ሰው ዕለት ዕለት በዓልን ያከብራል፡፡ ተስፋ መንግሥተ ሰማያት የተጠበቀለት ነው፡፡ ከሰማያዊው ማዕድና መጠጥ ተካፍሎ ሐሴት ያደርጋል፡፡ በዚኽ ምድር ላይ የሚደረጉ ጊዜያዊ ክንውኖች ስለቀረበት የኾነ ነገር እንደቀረበት አያስብም፤ ርሱ ያገኘው ከዚኽ በእጅጉ የሚልቅ ነውና፡፡ ነፍሱን ከሚያቆሽሹ ገቢረ ኀጢአቶች ራሱን ይጠብቃል፡፡

በገቢረ ኀጢአት ተሰማርተን ሳለ ሺሕ ጊዜ በዓላትን ብናከብር ግን እንዳከበርን ልንቈጥረው አይገባንም፡፡ ያከበርነው የበዓል ቀን (በዓል ማለት ደስታ ማለት ነው) ሳይኾን የኀዘን ቀን ነውና፡፡ ነፍሴ በኀጢአት ቀንበር ተይዛ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ሳለች የደስታን ቀን ባከብር ለእኔ ምን ጥቅም ያመጣልኛል? እግዚአብሔር የሚወዳችኁ እናንተም የምትወዱት ልጆቼ! አዲሱ ዓመት የእውነት አዲስ ዓመት እንዲኾንላችኁ ካሻችኁ ነፍሳችኁን ከኀጢአት ቀንበር አላቋት እንጂ ድጋሜ በኀጢአት ሸክም አትጫኗት፡፡ አሮጌው ዓመት እንዳለቀ ስታዩ እግዚአብሔርን አመስግኑት፡፡ ወደሌላ ዘመን አሸጋግሯቸዋልና እግዚአብሔርን አመስግኑት፡፡ ልቡናችኁንም ውቀሱት፡፡ በዕሜአችኁ ስንት ጊዜ እያለፈ እንደኾነ እያሰባችኁም ራሳችኁን እንዲኽ ብላችኁ ጠይቁት፡- “ቀናት እየሮጡ ነው፡፡ ዓመታቱም እየነጐዱ ነው፡፡ የዕድሜዬ መንገድም እየተጋመሰ ነው፡፡ ታድያ ምን በጐ ምግባር ያዝኩ? ከዚኽ ምድር የማልፍበት ቀን እየቀረበ ነው፡፡ ታድያ ምን የጽድቅ ሥራ ሠራኹ? በዚኽ ዕድሜዬ መሥራት የነበረብኝ ምግባር ትሩፋት ዕድሜዬ ሲገፋ ማድረግ አልችልም፡፡ ታድያ ዕድሜዬ ሲገፋ ማድረግ የማልችላቸውም የጽድቅ ሥራዎች (ፆም፣ ጸሎት፣ ስግደት፣ አገልግሎት፣… ዕድሜ ሲገፋ ይከብዳሉና) እንዳቅሜ እያደረግኩ ነውን?” ተወዳጆች ሆይ! አዲስ ዓመት ሲመጣ እነዚኽን ነገሮች በጥንቃቄ ልናስብባቸው ይገባናል፡፡ ይኽን እያደረግንም ስለቀጣዩ ዓመት እናስብ፡፡ ይኽን የምናደርግ ከኾነ “ቀኖቻቸውም በከንቱ አለቁ፤ ዓመቶቻቸውም በችኰላ” አይባልብንም /መዝ.78፡3/፡፡ ዕለት ዕለት በዓልን እናድርግ ብዬ የገለጥኩላችኹም ይኸው ነው፡፡ የእኛ በዓል ዘወትር መኾን ይገባዋል፡፡ የክርስቲያኖች በዓል በዓመታትና በቀናት ብቻ መወሰን የለበትም፡፡ ቤተ ክርስቲያንም በሳምንት፣ በወር፣ በዓመት የሚከበሩ በዓላት እንዲኖሩ ማድረጓ ዘወትር ከዚኹ ልንርቅ እንደማይገባ ማሳሰቧ እንጂ ሌላ አይደለምና፡፡ ይኽን በዓል በየዕለቱ ማድረግም ለኹሉም ይቻላል፤ ለድኻውም ለባለጸጋውም ይቻላል፡፡ በዓልን ለማድረግ (የጽድቅ ሥራን ሠርቶ ሐሴት ለማድረግ) የሚያስፈልገው ቅን ልቡና እንጂ ገንዘብ አይደለምና፡፡ ወዳጄ ሆይ! ገንዘብ የለኽምን? ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘብ አድርግ፡፡ ፈሪሐ እግዚአብሔርን ገንዘብ የምታደርግ ከኾነ ገንዘብ ካላቸው በላይ ባለጠጋ ነኽ፡፡ “እንዴት?” ትለኝ ይኾናል፡፡ እኔም እንዲኽ ብዬ እመልስልሃለኹ፡- የእነዚያ (የባለጠጐቹ) ገንዘብ ያልቃል፡፡ ያንተ ግን ብል አይበላውም፡፡ ጊዜ አይለውጠዉም፡፡ አያልቅም፡፡ ወደ ሰማያት፣ ወደ ሰማየ ሰማያት፣ ወደ ምድር፣ ወደ አየራት፣ ወደ እንስሳቱ ዓይነት፣ ብዙ የብዙ ብዙ ወደሚኾኑት ዕፅዋት፣ ወደ ደቂቀ አዳም በጠቅላላው፣ ወደ መላዕክት፣ ወደ መላዕክት አለቆች፣ ወደ ኀይላት ተመልከት፡፡ እነዚኽ ኹሉ የአምላክኽ ፍጥረቶች ናቸው፡፡ የእነዚኽን አምላክና መጋቢ ባርያ መኾን ድኻ መኾን አይደለምና ድኻ አይደለኽም ብዬ እነግርኻለኹ፡፡

ተወዳጆች ሆይ! ቀናትን ቈጥሮ በዓል ማድረግ የክርስቲያን ግብር አይደለም፤ የአሕዛብ ግብር እንጂ፡፡ እንዴት? የክርስቲያኖች ተፈጥሮ በቀንና በወር የተገደበ አይደለምና፡፡ አገራችን ሰማይ ነው፡፡ ግብራችን ሰማያዊ ነው፡፡ ኅብረታችንም ከሰማያውያን መላዕክት ጋር ነው፡፡ በዚያ መዓልት ለሌሊት ስፍራውን አይለቅም፡፡ ሌሊትም በተራው ለመዓልት አይለቅም፡፡ እዚያ ኹሌ መዓልት ነው፡፡ እዚያ ኹል ጊዜ ብርሃን ነው፡፡ ስለዚኽ “ከክርስቶስ ጋር ከተነሣችኁ ክርስቶስ በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጦ ባለበት በላይ ያለውን እሹ” እንደተባልን ኹል ጊዜ ማሰብ ያለብን ይኽንን ነው /ቈላስ.3፡1/፡፡ ክርስቲያናዊ ተፈጥሮአችን ከዚኽ ምድራዊ አቈጣጠር በላይ ነው፡፡ በንጽሕና በቅድስና እየኖርን ዘወትር በዓልን የምናከብር ከኾነም የዚኹ ዓለም ሌሊት ለእኛ ሌሊት አይደለም፤ መዓልት ነው እንጂ፡፡ ዘመናችንን በሙሉ በገቢረ ኀጢአት፣ በስካር፣ በዘፈን የምናሳልፈው ከኾነ ግን መዓልቱ ለእኛ መዓልት አይደለም፤ ሌሊት ነው እንጂ፡፡ ፀሐይዋ ብትወጣም ልቡናችን ገና በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይኖራልና ቀን እንደወጣ አይቈጠርም፡፡

ከገቢረ ኀጢአት ሳይወጡ አዲስ ዓመት ሲመጣ መደሰት፣ ብዙ መብልና መጠጥ ማዘጋጀት፣ አዲስ ልብስም መልበስ ጥቅም የለውም፡፡ ነፍሳችን በኀጢአት እየተጨነቀች፣ ነፍሳችን ተርባና ተጠምታ ሳለ፣ የተዳደፈ የኀጢአት ልብስም ተጆቡና ሳለ አዲስ ዓመት ማክበር ለእኛ ምን ጥቅም ይሰጠናል? እንዲኽ ከገቢረ ኀጢአት ሳይወጡ አዲስ ዓመትን ማክበር ማለት ለእኔ እንደ ልጆች የዕቃ ዕቃ ጨዋታ ነው፡፡

ክርስቶስ ከዚኹ ሥራ አውጥቶናል፡፡ ከሕፃንነት አዕምሮ ወደ ማወቅ አሸጋግሮናል፡፡ ከምድራውያን ለይቶ ከሰማያውያን ጋር ደባልቆናል፡፡ ስለዚኽ “መልካሙን ሥራችኁን ዐይተው በሰማያት ያለውን አባታችኁን እንዲያከብሩ ብርሃናችኁ እንዲኹ በሰው ፊት ይብራ” እንደተባለ አፍአዊ ሳይኾን መንፈሳዊውን ብርሃን ልናበራ ይገባናል /ማቴ.5፡16/፤ በአዲሱ ዓመት፡፡ ይኽም ብርሃን ተስፋ መንግሥተ ሰማያትን የሚያስገኝ ነው፡፡

ወዳጄ ሆይ! ቤቱ ቆሽሾ ሳለ ውጫዊ በሩን ብቻ ለማሽቀርቀር ለምን ትጨነቃለኽ? ነፍስኅ በኀጢአት ተዳድፋ ሳለ ሥጋኽን ብቻ ለማስደሰት ለምን ትሮጣለኽ? አስቀድመኽ ቤቱን (ነፍስኽን) ለማስዋብ አትሽቀዳደምምን? አስቀድመኽ ለነፍስኽ የምታስብ ከኾነ ከሰው እጅ ሳይኾን ከክርስቶስ እጅ ሹመት ሽልማት ትቀበላለኽ፡፡ ኹል ጊዜ “የማደርገው ነገር እግዚአብሔር ይከብርበታልን?” ብለኽ አስብ እንጂ እንዲኹ በዘልማድ የምትመላለስ አትኹን ብዬ እመክርኻለኁ፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ሲመክረን፡- “እንግዲኽ የምትበሉ ወይም የምትጠጡ ብትኾኑ ወይም ማናቸውም ነገር ብታደርጉ ኹሉን ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” ያለንም ስለዚኹ ነውና በአዲሱ ዓመት በድርጊቶቻችን ኹሉ እግዚአብሔርን ለማክበር እንዘጋጅ /1ኛ ቆሮ.10፡31/፤ አዲስ ዓመት ማክበር ማለት ይኼ ነውና፡፡

ለመኾኑ ለእግዚአብሔር ክብር ሲባል መብላት ወይም መጠጣት ማለት ምንድነው? ድኻውን ወደ ቤታችን ስንጠራው፤ በማዕዳችንም ክርስቶስ አብሮ ሲኖር ለእግዚአብሔር ክብር በላን ወይም ጠጣን ይባላል፡፡

ሐዋርያው የመከረን ግን በመብላችን ወይም በመጠጣችን ብቻ እግዚአብሔርን እንድናከብረው አይደለም፡፡ ጨምሮም “ማናቸውም ነገር ብታደርጉ ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት” አለን እንጂ፡፡ ስለዚኽ ወደ ሸንጐም ብንሔድ፤ ወደ ቤተ ክርስቲያንም ብንሔድ ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባናል፡፡ እነዚኽን ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ የምንችለውስ እንዴት አድርገን ነው? ወደ ቤተ ክርስቲያን፣ ወደ ሥርዓተ ቅዳሴው፣ ወደ ጉባኤው፣ ወደ ሌላውም አግልግሎት ስንሔድ አካሔዳችን እግዚአብሔር የሚከብርበት መኾን አለበት፡፡ እግዚአብሔር የማይከብርባቸው ብዙ ምልልሶች አሉና በአዲሱ ዓመት ወደ ቤተ ክርስቲያን መመላለሳችን ለእግዚአብሔር ክብር መኾን አለበት፡፡

ከቤት ቁጭ ማለትን የምንመርጥ ከኾነም ለእግዚአብሔር ክብር ልናደርገው ይገባናል፡፡ “ምን ማለት ነው?” ልትል ትችላለኅ፡፡ ከቤት ወጥተን ክፋት ወደ መላበት ሥፍራ፣ ክርክርና ክስ ወደ ሰፈነበት ሸንጐ፣ ዘፈን ስካርና ገቢረ ኀጢአት ወደሚደገስበት ነፍስንም ወደሚያውክ ስፍራ ከመሔድ ተቈጥበን ከቤት ቁጭ ብንል ለእግዚአብሔር ክብር አደረግነው ይባላል፡፡ ስለዚኽ ከቤት ውስጥ ቁጭ ማለትም ወደ ቤተ እግዚአብሔር መሔድም እኩል ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ይቻለናል ማለት ነው፡፡

በአዲሱ ዓመት ብናመሰግንም ብንገሥፅም ለእግዚአብሔር ክብር መኾን አለበት፡፡ “ለእግዚአብሔር ክብር ሲባል ማመስገንና መገሠፅ ሲባልስ ምን ማለት ነው?” ብሎ የሚጠይቅ ሰው ሊኖር ይችላል፡፡ እንበልና በመሥሪያ ቤታችን ቁጭ ብለናል፡፡ እጂግ ክፋትን የተመሉ ሰዎችም በፊታችን ይመላለሳሉ፡፡ እነዚኽ ሰዎች በውስጣቸው በትዕቢት፣ በቁጣ፣ እንዲኹም ይኽን በመሳሰሉ ጥገኛ ተሐዋስያን የተመሉ ናቸው፡፡ ነገር ግን እጂግ ውድ የኾኑ አልባሳትን ለብሰዋል፡፡ አከባቢውን የሚለውጡ ውድ የኾኑ ሽቶዎችን ተቀብተዋል፡፡ ይኽን እያየን ሳለ አንድ ሰው መጥቶ፡- “እንዴት የታደለ ሰው እንደኾነ ዐየኸውን? ደስ አይልም?” ሊለን ይችላል፡፡ እንዲኽ የሚላችኁን ሰው ገሥፁት፤ ምክሩት፤ ወይም ዝም በሉት፡፡ ቢቻላችኁ እዘኑለት (አልቁስለት)፡፡ ተግሣፅን ለእግዚአብሔር ክብር ማድረግ ማለትም ይኼ ነው፡፡

ተግሣፅ ሲባል ሰዎች ከነበሩበት የተሳሳተ አመለካከት ወጥተው ወደ ቀና አስተሳሰብ እንዲመጡ ማድረግ ነው፡፡ ከእንግዲኽ ወዲኽ ክፋትን ሳይኾን ምግባር ትሩፋትን እንዲያደንቁና እነርሱም ራሳቸው ለዚያ የተዘጋጁ እንዲኾኑ ማድረግ ነው፤ ተግሣፅ፡፡

ከላይ እንደነገርኳችኁ “እንዴት የታደለ ሰው እንደኾነ ዐየኸውን? ደስ አይልም?” ለሚላችኁ ሰው እንዲኽ በሉት፡- “ወዳጄ! ይኽ ሰው ንዑድ ክቡር ነው የምትለኝ ስለምንድነው? እጂግ ግሩምና ድንቅ የኾነች ሠረገላ (በዚኹ በ21ኛው መ/ክ/ዘ. የግል አውሮፕላን ወይም ሃመር መኪና ልንለው እንችላለን!) ስላለው ወይም ብዙ ሠራተኞችን (ብዙ ኩባንያዎችን ልንለው እንችላለን!) ስለሚያስተዳድር፣ እጂግ ውድ ውድ የኾኑ ፋሽን ልብሶችን ስለሚለብስ፣ በየዕለቱም የተለያዩ የመጠጥ ዓይነቶችን ስለሚጠጣና ቅንጡ የኾነ ሕይወትን ስለሚመራ ነውን? እውነት እውነት እልኻለኁ! ለዚኽ ሰውዬስ የዕድሜ ዘመን ዕንባ ያስፈልገዋል ብዬ እነግርኻለኁ፡፡ አንተ ርሱን የምታደንቀው አፍአዊ ነገሩን ብቻ በማየት ነው፡፡ አንተ ርሱን የምታደንቀው ግሩምና ድንቅ የኾነችውን ሠረገላው፣ ወይም ወርቃማው መጋለቢያውን፣ ወይም ልብሱን ዐይተኽ ነው፡፡ ይኽ ግን ለእኔ ምንም ነው፡፡ እስኪ ንገረኝ! ከዚኽ ሰው በላይ ጐስቋላ ሰው ማን አለ? ሠለገላው፣ መጋለቢያው፣ ልብሱ፣ እና ሌላው ሃብቱ እየተደነቀለት ሳለ ርሱ ግን ምንም ሳይመሰገን ቢሞት ከርሱ የባሰ ጐስቋላ ሰው ማን አለ ትለኛለኽ? ከዚኽ ዓለም ወደዚያኛው ዓለም ይዞት የሚሔድ ብዕል (ሃብት) ከሌለው ከዚኽ ሰው በላይ ድኻ ማን አለ? ከአፍአ ሲታይ እጂግ የሚያምርበት ከውስጡ ግን የተለሰነ መቃብር ከኾነው ከዚኽ ሰውዬ በላይ ጐስቋላ ሰው ማን አለ? የእኛ የክርስቲያኖች ትክክለኛ ሃብት ጌጣ ጌጥ፣ ወይም ሠራተኞቻችን ወይም ልብሳችን ወይም ሠረገላዎቻችን አይደሉም፡፡ የእኛ ትክክለኛ ሃብት ምግባር ትሩፋታችን ነው፡፡ የእኛ ሃብት በእግዚአብሔር ማመናችንና መታመናችን ነው፡፡”

ዳግመኛም እጅግ ድኻ፣ በጓደኞቹ ዘንድ ዕድሜውን በሙሉ እንደ ፋራና ያልዘመነ ሰው የሚቈጠር፥ ግን ደግሞ በምግባር በትሩፋት ያጌጠ ሰውን ብታዩ ይኽ ሰው ንዑድ ክቡር ሰው ነው ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡ ምንም በዚኽ ምድር ላይ ያፈራውና ያጠራቀመው ሃብት ባይኖሮውም በሰማያት ዘንድ ድልብ ሃብት አለውና ይኽ ሰው በእውነት ንዑድ ክቡር ነው ብዬ እነግራችኋለኹ፡፡

ይኽን አመለካከት ስለያዛችኁ ብቻ ጓደኞቻችኁ፡- “ኧረ በሥሉስ ቅዱስ! ይኽ ሰውማ እጅግ የተረገመ ሰው ነው!” ቢልዋችኁ፥ “እንደዉም እንደዚኽ ሰው ንዑድ ክቡር የለም፡፡ ወዳጅነቱ ከኃላፊውና ጠፊው ሃብትና ንብረት ሳይኾን ከእግዚአብሔር ጋር ነውና ንዑድ ክቡር ነው፡፡ ዕድሜውን በሙሉ ሲያከማች የነበረው እንደ እኛ አፍአዊውን ሳይኾን ብልና ዝገት የማያገኘውን ብዕል ነበርና ንዑድ ክቡር ነው፡፡ የዚኹ ሰው ሀብቱ በትዕቢት፣ በቁጣ፣ በዘፈን፣ በስካርና በገቢረ ኀጢአት ያልቆሸሸ ንጽሐ ልቡናው ነውና ንዑድ ክቡር ነው፡፡ እስኪ ንገረኝ! ይኽ ሰው ግሩምና ድንቅ የኾነች ሠረገላ፣ በወርቅ የተሽቆጠቆጠ መጋለቢያ፣ ውድ ውድ የኾኑ አልባሳት ስለሌለው የተጐዳ ይመስልኻልን? ርስት መንግሥተ ሰማያትን ከማግኘት በላይ ሌላ ምን ሃብት አለ ብለኽ ልትነግረኝ ትችላለኽ?” ብላችኁ መልሱላቸው፡፡

እግዚአብሔር የሚወዳችኁ እናንተም የምትወዱት ሆይ! በአዲሱ ዓመት ብቻ ሳይኾን ዘወትር እንዲኽ እግዚአብሔርን በሚያስከብር መንገድ የምንገሥፅ፣ ወይም የምናመሰግን ከኾነ ሹመት ሽልማታችን ብዙ ነው፡፡

ልጆቼ! ይኽን ኹሉ የምነግራችኁ እንዲኹ ስሜታችኁን ለማርካት አይደለም፡፡ ይልቁንም በአዲሱ ዓመት ብቻ ሳይኾን በየዕለቱ አስተሳሰባችንን እንዲኽ የምናስተካልለው ከኾነና እኛም እንደዚኹ በምግባር በትሩፋት ለማጌጥ የምንሽቀዳደም ከኾነ ሹመት ሽልማታችን ብዙ የብዙም ብዙ መኾኑን ለማስረዳት ነው፡፡ ነቢየ እግዚአብሔር ክቡር ዳዊት ስለዚኹ ጕዳይ ምን እንደሚል እስኪ አብረን እናድምጠው፡- “በአንደበቱ የማይሸነግል፣ በባልንጀራው ላይ ክፋትን የማያደርግ፣ ሰርቆ ቀምቶ እናት አባቱን የማያሰድብ፣ እኩይ ምግባር በፊቱ የተናቀለት፣ እግዚአብሔርንም የሚፈሩትን የሚያከብር፣ ለባልንጀራው ምሎ የማይከዳ፣ ገንዘቡን በአራጣ የማያበድር፣ ከድኻው መማለጃን የማይቀበል፣ እንዲኽ የሚያደርግ ሰው በመከራ ሥጋ መከራ ነፍስ ለዘለዓለም አይታወክም” /መዝ.15፡3-5/፡፡ ይኽም ማለት ክፋትን በመጸየፍ በጐውንም በማመስገን እግዚአብሔርን የሚያከብር ሰው ነፍሱ ለዘለዓለም አትታወክም ማለት ነው፡፡ ዳግመኛም ይኼ ክቡር ዳዊት በሌላ ሥፍራ እንዲኽ አለ፡- “አቤቱ ባለሟሎችኅ በእኔ ዘንድ እንደምን እጅግ ንዑዳን ክቡራን ናቸው! አስቀድመው ከነበሩት ባለሟሎችኅ ይልቅም እኒኽ ፈጽመው ጸኑ!” /መዝ.139፡17/፡፡

እግዚአብሔር ያከበረውን ግን አትገሥፁ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር በጽድቅ በቅድስና ሕያዋን የኾኑትን ያከብራልና፡፡ በሰው ዓይን እዚኽ ግቡ የማይባሉ ድኾች ቢኾኑም በእግዚአብሔር ዘንድ ንዑዳን ክቡራን ናቸውን እነዚኽን አትገሥፁ፡፡ እግዚአብሔር ያላከበረውን ግን ገሥፁት፡፡ ምንም ያኽል በወርቅ ላይ ቆሞ በወርቅ ላይ ቢተኛም ምግባር ትሩፋትን ሳይይዝ በገቢረ ኀጢአት የፀናውን፣ በሚቀጥለው ዓመትም ይኽን ለማድረግ የሚያቅደውን ሰው ገሥፁት፡፡ በአጭር ቃል ስታመሰግኑም ስትገሥፁም ለእግዚአብሔር ክብር አድርጉት፡፡ አዲስ ዓመትን ማክበር ማለት እንደዚኽ በኹለንተናችን አዲስ ሰው ኾኖ በመዘጋጀት ነውና፡፡