ማኅሌተ ጽጌ፤ ምንጩ ትርጉሙና መልእክቱ (ክፍል አንድ)

በዲ/ን ያረጋል አበጋዝ

(መቅረዝ ዘተዋሕዶ፣ መስከረም 25 ቀን፣ 2007 ዓ.ም.)፡-በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ኃይለ ቃልን ከትርጓሜ፣ ትርጓሜንከምሥጢር እንዲሁም ደግሞ ምሥጢርን ከዜማ ጋርአስተባብረውና አስማምተው የሚደርሱ ሊቃውንት ባለቤትናት፡፡ በ5ኛው መ.ክ.ዘመን የተነሣው ታላቁ ሊቅ ቅዱስ ያሬድአምስቱን ጸዋትወ ዜማ ሲደርስ በ14ኛው መ.ክ.ዘመንየተነሣው አባ ጊዮርጊስ ደግሞ ሰዓታትን ደርሷል፡፡ በዚሁ ዘመንአባ ጊዮርጊስ ጋር ጥልቅ መንፈሳዊ ፍቅር የነበረው አባ ጽጌድንግል “ማኅሌተ ጽጌ” የተባለውን ድርሰት ደርሷል፡፡ ማኅሌተጽጌ ግጥማዊ አካሔድ ያለው ድንቅ ኢትዮጵያዊ ድርሰት ነው፡፡ይህ ድርሰት በማንኛውም ጊዜ የሚጸለይ ቢሆንም በተለየ ሁኔታበቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የሚውለው ከመስከረም 26 እስከኅዳር 5 ቀን ድረስ ባለው የእመቤታችን የቅድስት ድንግልማርያም የስደት ዘመን ነው፡፡ በዚህ ወቅት በየሳምንቱ እሑድሌሊት በሙሉ የእመቤታችንን ከልጇ ጋር ወደ ግብፅ መሰደድናመንከራተት እያሰቡ የሚደረስ ምሥጋናና ጸሎት ነው፡፡

በሀገራችን የመስከረምና የጥቅምት ወራት የአበባ ወራት /ዘመነ ጽጌ/ ናቸው፡፡ ይህም ወቅት ተራሮች በአበባየሚያጌጡበትና ለዓይን ማራኪ የሚሆኑበት ጊዜ ነው፡፡በዚህም ዘመን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “ስለልብስስ ስለምን ትጨነቃላችሁ? የሜዳ አበቦች እንዴትእንዲያድጉ ልብ አድርጋችሁ ተመልከቱ፡፡ አይደክሙም፣አይፈትሉም፤ ነገር ግን እላችኋለሁ ሰሎሞንስ እንኳ በክብሩሁሉ ከእነዚህ እንደ አንዱ አልለበሰም፡፡ እግዚአብሔርን ዛሬያለውን ነገም ወደ እቶን የሚጣለውን የሜዳን ሣር እንዲህየሚያለብሰው ከሆነ እናንተ እምነት የጐደላችሁ እናንተንማይልቁን እንዴት እንግዲህ ምን እንበላለን ምንስ እንጠጣለን?ምንስ እንለብሳለን? ብላችሁ አትጨነቁ ...» /ማቴ.5፡28-33/በማለት የተናገረውን ቃል በማሰብ መጨነቅ የሚገባንመንግሥተ ሰማያት ለመግባት እንጂ በዚህ ዓለም ስላለው ነገርእንዳልሆነ ተራሮችን በአበባ ያለበሰ አምላክ በአርአያውናበአምሳሉ የፈጠረንን እኛን ለኑሮ የሚያስፈልገንን ምግብናልብስ እንደማይነሳን እያሰብን የምንዘክርበት ወቅት ነው፡፡እንዲሁም ክቡር ዳዊት «ተዘከር እግዚኦ ከመ መሬት ንሕነሰብእሰ ከመ ሳዕር መዋዕሊሁ ወከመ ጽጌ ገዳም ከማሁ ይፈሪ፤አቤቱ እኛ አፈር እንደሆን አስብ ሰውስ ዘመኑ እንደሣር ነውእንደ ዱር አበባ እንዲሁ ያብባል ነፋስ በነፈሰበት ጊዜያልፋልና» /መዝ.1ዐ2፤14-16/ በማለት እንደ ተናገረው የሰውሕይወት በሣር ይመሰላል፡፡ ሣር አድጐ አብቦ ከዚያ በኋላይደርቅና በነፋስ አማካኝነት ያ የረገፈው ሣር እየተነሣየነበረበት ቦታ ስንኳ እስከማይታወቅ ድረስ ይሆናል፡፡ ሰውምከአደገ በኋላ በሕማም ፀሐይነት ይደርቅና በሞተ ነፋስነትይወሰዳል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደ መቃብር ሲወርድ የነበረበት ቦታይዘነጋል፡፡ ስለዚህ ዘመነ ጽጌ ሰው ዘመኑ እንደ አበባ በቶሎየሚረግፍ መሆኑን በማሰብ ይህ ዘመን ሳያልፍ መልካም ሥራለመሥራት ትንሣኤ ኅሊና የሚነሣበት ጊዜ ነው፡፡ ቅዱስ ያሬድለዘመነ ጽጌ የሠራው ድጓም ይህንኑ የሰውን ዘመን አጭርነት የሕይወቱን ኢምንትነት በዚህ ሕላዌ የተፈጠረ ሰው በዚህዓለም ክፉ ሥራ መሥራት እንደሌለበት ሁልጊዜ በተዘክሮተሞት እንዲኖር የሚያስረዳ ነው፡፡

በዘመነ ጽጌ ቅዱስ ያሬድ ከደረሰው ድጓ በተጨማሪ ከላይእንደተጠቀሰው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የተነሣ አባ ጽጌድንግል ከዚሁ ዘመን ጋር የተያያዘ ድርሰት ደርሷል፡፡ ይህድርሰት በግጥም መልክ የተደረሰ በአብዛኛው አምስት ስንኞችያሉት ሲሆን ብዛቱም 15ዐ ያክል ነው፡፡ ይህም ድርሰት«ማኅሌተ ጽጌ» በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ፍሬ ከአበባአበባም ከፍሬ እንደሚገኘው ሁሉ ማኅሌተ ጽጌም እመቤታችንቅድስት ድንግል ማርያምንና ልጇን መድኃኒታችንናአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስን በአበባና በፍሬ እየመሰለየሚያስረዳ ድርሰት ነው፡፡ እርሷን በአበባ ሲመስል ልጇን በፍሬእርሷን በፍሬ ሲመስል ደግሞ ልጇን በአበባ እየመሰለይናገራል፡፡ ነቢዩ ኢሳይያስ «ትወጽእ በትር እምሥርወ እሴይወየዓርግ ጽጌ እምጉንዱ፤ ከእሴይ ግንድ በትር ይወጣል፤ከሥሩም ቁጥቋጦ ያፈራል» /ኢሳ.11፡1/ ብሎ ከእሴይ ዘርየምትገኘውን እመቤታችንን በበትር ከርሷ የሚገኘውንክርስቶስን ደግሞ በጽጌ መስሎ ትንቢቱን ተናግሯል፡፡ አባ ጽጌድንግልም ድርሰቱን በዚሁ አንጻር በመቀመር እያንዳንዱንመልክዕ እመቤታችንንና ልጇን አስተባብሮ በጽጌና በፍሬበመመሰል የእግዚአብሔርን ድንቅ ሥራ በምሥጢር በታሪክ፣በጸሎትና በመሳሰለው መልክ ድንቅ በሆነና በተዋበ ሁኔታአዋሕዶ ደርሶታል፡፡

እመቤታችን ጣዕሟንና ፍቅሯን እንዲሁም ምስጋናዋንሲናፍቁ የነበሩትን ቅዱስ ኤፍሬምንና አባ ሕርያቆስንውዳሴዋንና ቅዳሴዋን እንደገለጸችላቸው ለፍቅሯ ሲሳሳለነበረው ለአባ ጽጌ ድንግል ደግሞ ይህንን ማኅሌተ ጽጌንእንዲደርስ አድርጋዋለች፡፡ ከላይ እንደተገለጸው ማኅሌተ ጽጌበመልክዕ አደራረስ ሥርዓት የተደረሰ ሲሆን ይህንንምለመመልከት እንዲያመች በሚከተሉት ክፍሎች ከፋፍሎማቅረብ ይቻላል፡፡

1. ጸሎት

በዚህ አገባብ ጸሎት ስንል በተለየ ሁኔታ ጸሎትነቱ የጐላውንለማየት እንጂ ድርሰቱ በሙሉ ጸሎት ነው፡፡ ሌሎቹንም እንዲሁታሪክ፣ ተግሳጽ፣ ምሥጢር ተብለው መከፈላቸው በበዛውናበጐላው ለመግለጽ ነው እንጂ ሁሉም በሁሉ አለ፡፡በጸሎትነታቸው ጐልተው ከሚታዩት ውስጥ የተወሰኑትንእንመለከታለን፡፡

1.1. አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፣
ወከመ ማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት፣
በእንተ ርስሐትየሰ ኢትመንንኒ ንግሥት፣
እስመ ወሀብኩ ንብረትየ ለፍቅርኪ ሞት፣
ዘአሰገርዎሙ ለሰማዕት በጽጌሁ ሕይወት፡፡

ጠቢቡ ሰሎሞን «የምእመናንንና የክርስቶስን ነገር በምሥጢርበተናገረበት በመኃልይ መጽሐፉ «እንደ ማኅተም በልብህ እንደማኅተም በክንድህ አኑረኝ» /መኃ.9፤6/ ይላል፡፡ ይኸውምየምእመናንንና የክርስቶስን አንድነት የሚገልጽ ነው፡፡«አንብርኒ ማርያም ውስተ ልብኪ ከመ ሕልቀት፤ ወከመማዕተብ ፁርኒ በመዝራዕትኪ ልዕልት» ማለቱ እመቤታችንንእንደ ማኅተም በልብሽ አኑሪኝ በማለት በእናትነትሽ፣በአማላጅነትሽ አትርሽኝ ካለ በኋላ «በእንተ ርስሐትየሰአትመንኒ ንግሥት» ይላል፡፡ ይኸም ማለት አትርሽኝ በልብሽአኑሪኝ ብዬ የምለምንሽ አንቺ እንዳትረሽኝ የሚያደርግመልካም ሥራ ኖሮኝ አይደለም፡፡ ስለዚህ በሰውነቴ ክፋትምክንያት በኃጢአቴና በወራዳነቴ ምክንያት እኔን ከማሰብከልቡናሽ አታውጪኝ በማለት እመቤታችን በርኅሩኅ ልቧ«መሐር ወልድየ ወተዘከር ኪዳንየ» እያለች እንድታዘክረንየሚያሳስብ ጸሎት ነው፡፡

ሶበ አተቦ ለማይ በቅዳሴኪ እንዘ ይጼሊ፣
ረሰዮ ኅብስተ ጽጌ ሃይማኖት ሳሙኤል ዘሐቅለ ዋሊ፣
ምሕረተ ወፍትሐ ለተአምርኪ አኀሊ፣
ሥረዪ ኃጢአትየ ወእጸብየ አቅልሊ፣
እስመ ኩሉ ገቢረ ማርያም ትክሊ፡፡

አባ ሳሙኤል ዘዋልድባ ቅዳሴ ማርያምን እየደገሙ ውኃውበተአምራት ኅብስት ይሆንላቸው ነበር፡፡ ይህን ተአምርከአደነቀ በኋላ «ማርያም ሆይ ሁሉን ማድረግ ትችያለሽናኃጢአቴን አስተስርይልኝ» ይላል፡፡ ጌታችን «እውነት እላችኋለሁየሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገርየለም» /ማቴ.17፡1/ በማለት ላመነ የሚሣነው ነገር እንደሌለተናግሯል፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም መልአኩ«ትጸንሻለሽ፣ ትወልጃለሽ ...» ብሎ ባበሠራት ጊዜ ይህእንደምን ይሆንልኛል? ብላ ስትጠይቅ «ለእግዚአብሔርየሚሳነው ነገር የለም» ሲላት በፍጹም እምነት ይኩነኒ በከመትቤለኒ እንደቃልህ ይሁልኝ» በማለት የተቀበለች ናት፡፡ይህንንም ቅድስት ኤልሳቤጥ መንፈስ ቅዱስን ተመልታ «ከጌታየተነገረላት ቃል ይፈጸማልና የታመነች ብፅዕት ናት» /ሉቃ.1፡453 ብላ መስክራለች፡፡ ላመኑ ሁሉ የሚቻል ከሆነእመቤታችን ግን ቅዱሳን ሁሉ የሚማጸኑትን አምላክ በሥጋወልዳ ያስገኘች ስለሆነች ለእርሷ የሚሳናት ነገር የለም፡፡ስለዚህም ነው ላንቺ የሚሳንሽ ነገር የለምና ኃጢአቴንአስተስርዪልኝ፣ የከበደኝን ሁሉ አቅልይልኝ በማለትየለመነው፡፡

1.2. «ተአምርኪ ማርያም ተሰብከ በኦሪት፣
አመ ተሰነዓውኪ ጳጦስ ምስለ መለኮት፣
ዘርእየኪ ሙሴ ሊቀ ነቢያት
ጸልልኒ በአዕፁቅኪ ሐመልማላዊት ዕፀት
ሦከ ኃጢአትየ ያውዒ ጽጌኪ እሳት፡፡

«ማርያም ሆይ ነበልባል ከሐመልማል ተዋሕዶ ሙሴ በደብረኮሬብ ባየ ጊዜ ተአምርሽ በኦሪት ተሰበከ ተነገረ፡፡ ምሳሌሽበሐመልማልና በእሳት አምሳል የታየ ማርያም ሆይ ጽጌ ልጅሽኃጢአቴን ያጠፋልኝ ዘንድ በጥላሽ ሥር አስጠጊኝ፡፡”

ሙሴ በምድያም በስደት ሆኖ የአማቱን የዮቶርን በጎችእየጠበቀ ሳለ በኮሬብ ተራራ ድንቅ ራእይ ታየው፡፡ቁጥቋጦው በእሳት ሲነድ፡፡ ቁጥቋጦውም ሳይቃጠል አየ፡፡ዘጸ.3፡3፡፡ ይህ የምሥጢር ተዋሕዶ ተምሳሌታዊ ራእይ ነበር፡፡ሐመልማል የእመቤታችን ምሳሌ ሲሆን እሳቱ ደግሞ የመለኮትምሳሌ ነው፡፡ የሐመልማሉ ርጥበት እሳቱን አለማጥፋቱአምላክ ሰው ሲሆን ከመለኮቱ ክብር ዝቅ ያለማለቱ ምሳሌነው፡፡ እሳቱ ደግሞ ሐመልማሉን አለማቃጠሉ መለኮትከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነሥቶ በተዋሐደጊዜ እንዳጸናትና እንዳደረገችው የሚያስረዳ ነው፡፡

ደራሲው የእመቤታችን ክርስቶስን የማስገኘት ተአምርናየእርሷ የአምላክ እናት መሆን ከጥንት ጀምሮ ሲነገር የኖረመሆኑን ካስታወሰ በኋላ ጸሎቱን «ጸልልኒ በአዕፁቅኪሐመልማላዊት ዕፀትኮ ሦከ ኃጢአትየ ያውኢ ጽጌኪ እሳት»በማለት ያቀርባል፡፡ ይኸም ማለት «ያ ከሐመልማል ጋርተዋሕዶ የታየው እሳት ጽጌሽ/ ልጅሽ ክርስቶስ/ ኃጢአቴንይቅር ይለኝ ዘንድ በአንቺ ሐመልማልነት አስጠጊኝ” ማለትነው፡፡

ዳዊት «በአንቺ የሚኖሩ ሁሉ ደስ ይላቸዋል» /መዝ.86፡7/ ብሎእንደተናገረ በእመቤታችን እናትነትና አማላጅነት ጥላ ሥርየሚኖሩ ከልጇ ከክርስቶስ ሥርየተ ኃጢአትን አግኝተው፣በመንፈስ ቅዱስ ጸጋ ተጐብኝተው ደስተኞች እንደሚሆኑየተናገረው ትንቢት መፈጸሙን የሚያስረዳ ነው፡፡

ይቀጥላል…