ለተገደለው Mr. GEORGE FLOYD የተሰማን ጥልቅ ኀዘን

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን!

ክርስቶስ ተንሥዓ እሙታን!
ግንቦት ፳፫/፳፻፲፪ ዓ/ም

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ርእሰ አድባራት ጽርሐ-አርያም ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እና በውስጥዋ የምንኖር መላው ካህናት እና ምዕመናን በዘግናኝና አሰቃቂ እንዲሁም ፍጹም ኢሰብዓዊ በሆነ ሁኔታ ሰኞ ግንቦት ፲፯/፳፻፲፪ ዓ/ም (May 25, 2020) በግፍ ለተገደለው Mr. George Floyd የተሰማንን ጥልቅ ኀዘን በውስጣችን ይዘን ሳንናገረው በዝምታ የምናልፈው ስላይደለ ከዚህ እንደሚከተለው እንገልጻለን።

እጁን የፊጥኝ ታስሮ፣ ዕግሩ እንዳይላወስ በግድ ተይዞ፣ የደም ቱቦ መተላለፊያው አንገቱ ላይ ለስምንት ደቂቃ ከአርባ ስድስት ሰከንድ ያህል ከመሬቱ ጋር በጨካኝ ሰው ጉልበት ተሰፍቶ ምንም መላወስ በማይችልበት ሁኔታ ውስጥ በሚያሳዝን ሲቃ «እባክህ መተንፈስ አልቻልኩም፤ ሆዴ፣ አንገቴና ሁለመናዬ ተጎድቷል፤ ሊገድሉኝ ነው» እያለ ሲጮህ መልስ አልባ የነበረው የ፵፮ ዓመት ሰው ከዚያ ሁሉ ሥቃይ በኋላ ከሞት የሚያስጥለው ወገን አጥቶ መከራውንና ሥቃዩን ለብቻው ታግሎ ትንፋሽ አልባ ሆኖ ላይመለስ አሸልቧል። ከልመና በስተቀር አንዳች ማድረግ እንደማይቻል ተረድቶ በተደጋጋሚ ቢማጸንም ያቺ ቀን ነፍሱ ከሥጋው የምትለይባት በመሆኗ የሞት ጽዋ ከመቅመስ የልመና ቃሉም ሆነ አሳዛኝ ሲቃው ሳይራዱት ቀሩ።

ይኽ ዜና ተደብቆ የማይቀር ሆነና በተለያዩ ማኅበራዊ ድረ ገጽ ላይ ወጥቶ ለሕዝብ ዕይታ ሲደርስ በቀን በአደባባይ እንዲህ ያለው ድርጊት መፈጸሙ በጠቅላላው የዓለምን ሕዝብ በተለይም መላው አሜሪካንን ክፉኛ አስቆጣ። በእያንዳንዱ ቤት ውስጥ እንዲሁም በእያንዳንዱ ዓይንና ጆሮ የዚህ ጭከና የተሞላበት ግድያ መድረሱ፣ መታየቱና መሰማቱ በወላጆችና በልጆች መካከል ጥያቄ አጫረ። ክቡር የሆነና በእግዚአብሔር እጅ ተፈጥሮ የእግዚአብሔር እስትንፋስ በውስጡ ያለበት «ሰው» የሚባል ፍጥረት በሕይወት መኖሩ ለክፉዎች እንደ ምንም ተቆጥሮ ነፍሱ ስትነጠቅ ማየት በሁሉ ዘንድ ታላቅ ስጋትን ፈጠረ።